“አንድነታችን የአብሮነታችን እና የታሪካችን ምንጭ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ

41

ደሴ: ኅዳር 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር 18ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓልን “ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የክፍለ ከተማ የሥራ ኀላፊዎች፣ የደሴ ከተማ ምክር ቤት አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ደሴ ከተማ ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርባት፤ ሙስሊም ክርስቲያኑ በፍቅር እና በአድነት የሚኖርባት የመተሳሰብ ከተማ ነች ብለዋል። ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዓሉ ሲከበር የአንድነት ገመድን አጥብቆ በመያዝ ሊኾን እንደሚገባም ነው ያብራሩት።

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን ከጥፋት እንዲመለሱ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከጎጠኝነት አስተሳሰብ እንዲወጣ ለማድረግ ላደረጋችሁት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ምሥጋና ይገባችኋል ነው ያሉት። አንድነታችን የአብሮነታችን እና የታሪካችን ምንጭ ነው ብለዋል ከንቲባ ሳሙኤል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል። የደሴ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ አሕመድ ሙህዬ የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል መከበር የተለያዩ ሕዝቦች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጉላት ያስችላል ብለዋል።

ዘጋቢ:-ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሐሰተኛ ማኅተሞችን በማተም የተለያዩ ማስረጃዎችን ሲሰጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ ገለጸ።
Next article“ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት” አቶ ደመቀ መኮንን