
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሐሰተኛ ማኅተሞችን በማተም የተለያዩ ማስረጃዎችን ሲሰጡ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወካይ ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ያረጋል ተሻለ እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ ግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ 143 ልዩ ልዩ ማኅተሞችን፣ 112 የተለያዩ ግለሰቦች የቀበሌ መታወቂያዎችን መያዝ ችሏል።
ከዚህም ባለፈ መሸኛ፣ የነዋሪዎች መታወቂያ፣ ያላገባ፣ የተመላሽ ሠራዊት ማስረጃዎች፣ የቀበሌ ቤት ውል፣ ካርታ እና ፕላን፣ የቤት ማኅበር ማስረጃ፣ የወሳኝ ኩነት፣ የልደት ካርድ የመሳሰሉ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ተወካይ ኀላፊው ገልጸዋል።
ማኅተሞች በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ቀበሌዎች በተለያዩ አመራሮች እና ባለሙያዎች ስም የታተሙ ናቸው። ተጠርጣሪዎችም በፖሊስ ቁጥጥር ውለው ምርመራ እየተደረገ መኾኑን ኢንስፔክተር ያረጋል ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ ሕገ ወጥ አሠራርን ሲመለከት ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል። ቤት አከራዮችም የሚያከራዩትን ግለሰብ ማንነት ክትትል እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!