
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ወራት በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ሳንካዎችን ፈጥሯል፡፡ የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ኹኔታ አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ከሰላም አማራጮች እና ጥሪዎች ጎን ለጎን የተሠራው ሕግ የማስከበር ሥራ ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡ በበርካታ አካባቢዎች አሥተዳደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎቹ ወደ መደበኛ ኹኔታ እንዲመለሱ እየተደረጉ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ከምንም በላይ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የማስጠበቅ ቀዳሚ ኀላፊነት ነበረበት ያሉት አቶ ይርጋ ከሞላ ጎደል ችግሮችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ሥር-ነቀል ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል፡፡ ተዳክሞ የነበረውን የፖለቲካ እና የፀጥታ መዋቅር በሚገባ በመፈተሽ አስፈጻሚውን አካል መልሶ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች የፀጥታ መዋቅሩ እና የፖለቲካ አመራሩ ዋጋ እየከፈሉም ቢኾን ለሕዝብ ነጻነት እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ አጋርነት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥረት እና የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ብርታት የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ በኩል ስኬታማ ሥራዎችን ሠርተዋል ነው ያሉት፡፡
ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን በተለያዩ አጀንዳዎች ተስበው ወደ ግጭት የገቡ ወንድሞቻችን የሰላም እድል እንዲያገኙ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ተደርጓል ያሉት አቶ ይርጋ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እውነቱን የተረዱ በሰላማዊ መንገድ እየገቡ ነው ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ምክክሮች በተሳሳተ መንገድ የገቡ ወንድሞቻችንን ለመመለስ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ሕግ ከማስከበሩ ጎን ለጎን ለምን የሰላም አማራጮች በሙሉ አቅም አይታዩም የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው አቶ ይርጋ ሲመልሱ የክልሉ መንግሥት ከግጭቱ በፊት ሳይቀር የሰላም አማራጮች በአግባቡ እንዲታዩ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ለማሳያነትም “የክልሉ መንግሥት ለሰላም ባለው ቁርጠኝነት በምክር ቤት ሳይቀር የሰላም ሞሽን ሞክሮ ነበር” ብለዋል፡፡
አሁንም የሰላም አማራጮች በመንግሥት በኩል ዝግ አይደሉም፤ ኾነውም አያውቁም ያሉት አቶ ይርጋ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እና ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀው ለሚገቡ ሁሉ የሰላም በሮች ክፍት ናቸው ብለዋል፡፡ በክልሉ አንድ አንድ አካባቢዎች አሁንም ድረስ የሚስተዋሉት በሕዝብ ላይ ሽብር እና ወከባ የመፈጸምን ሂደት ግን በትዕግስት አንመለከትም ነው ያሉት፡፡
አቶ ይርጋ በመግለጫቸው ከቀበሌ መዋቅር እስከ ፌደራል መንግሥት ድረስ መልስ የሚያስፈልጋቸው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እና ለማስመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለማስመለስም ከሕግ ማስከበር እና የሰላም አማራጮች ጎን ለጎን በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹን ስትራቴጂክ ጉዳዮች ውጤታቸውን ለሕዝብ በአስፈላጊ ጊዜ እናሳውቃለን ብለዋል።
በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር መልኩም ኾነ የሚሳተፈው እጅ ብዙ በመኾኑ በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ ያነሱት አቶ ይርጋ አላስፈላጊ መሥዋዕትነት ቢከፈልም የክልሉ ሕዝብ እውነታውን እየተረዳ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም የጤና፣ የግብርና እና የትምህርት ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመፈጸም ለክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!