
አዲስ አበባ: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ አየር ኀይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የመከላከያ ሠራዊት የተመሰረተው የካቲት 7/1887 ነበር። ይህም የመከላከያ ሠራዊት የተመሰረተበት ቀን ኾኖ ይከበራል። ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ የአየር ኀይል ቀን ይከበር የነበረ ሲኾን ይህን ለማረም እና አየር ኀይሉ የተመሰረተበትን ቀን ለማሰብ ቀኑ እንዲከበር መወሰኑን ተናግረዋል።
የአየር ኀይል ከሕዳር 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ነው የሚገኘው። የፊታችን ታኅሣሥ 6/2016 ዓ.ም ደግሞ ማጠቃለያውን ያገኛል ነው የተባለው።
ከጣሊያን ሁለተኛ ዙር ወረራ በኋላ ንጉሱ አጼ ኃይለሥላሴ ሕዳር 20/1928 ኢትዮጵያዊ አየር ኀይል አዛዥ የሾሙበት እለት ነው። የአየር ኀይልም ለመጀመሪያ ጊዜ ስያሜ ያገኘበት ዕለት እንደኾነ የሰነድ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ቀን የኢትዮጵያ አየር ኀይል ስያሜ የተሰጠበት እና አዛዥ የተሾመበት በመኾኑ ቀኑ በምክንያት አየር ኀይል የተመሠረተበት ቀን መኾኑ ከግንዛቤ ገብቶ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
በዓሉ የሚከበርበትን ምክንያት ሲያብራሩ አየር ኀይል ባደረገው ሪፎርም የተጨበጠ ለውጥ ያመጣ መኾኑን አንስተዋል። ተቋሙ በአንድ ትውልድ ተመስርቶ የሚያልቅ ባለመኾኑ አሁን ያለውን አቅም ማጎልበት እና ለቀጣይ ትውልድ አዘጋጅቶ የማስረከብ ሂደትም ነው ብለዋል።
በርካታ ተቋማትም ለአየር ኀይል ተቋማዊ ግንባታ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ሊመሠገኑ ይገባል ነው ያሉት። ባለሀብቶች እና የመንግሥት ተቋማትም ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።
አየር ኀይሉ ከአባል እስከ አዛዥ አሁን ለመጣው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው በመኾኑ በበዓሉ ማመሥገን እና ማክበር አስፈልጓል ብለዋል።
አየር ኀይል በተለያየ መንገድ የሰው ኀይሉን ሲያበቃ ቆይቷል ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ ተወዳዳሪ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና የሚረዳ እንዲኾን ነባሩን የማሠልጠን እና አዲሰ ሠራዊት በሚገባ ማብቃት ተችሏል ብለዋል። ሠራዊቱ አሁን ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገለግል ተቋም እንዲኾን አድርጎ መገንባት ተችሏል ነው ያሉት።
በአከባበሩም ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጣዩ የአየር ኀይል አዛዦች ኦፊሰር ይመረቃሉ ተብሎም ይጠበቃል። ኦፊሰሮቹ የበረራ ሰዓታቸውን ያሟሉ ለ3 ዓመታት ሲገመገሙ የቆዩ በቀጣይ አየር ኀይሉን መምራት የሚችሉ ኦፊሰሮች እንደኾኑም አስረድተዋል።
የትራንስፖርት አውሮፕላኖች፣ ተዋጊ ጀቶች፣ ሄሌኮፍተሮችን በማደስ እና ዲጂታላይዝ በማድረግ ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል። አዳዲስ ተዋጊ ጀቶችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አየር ኀይሉ በግዥ መታጠቁን ተናግረዋል።
በማጠቃለያ ዕለቱም ጥቁር አንበሳ የተሰኘ የአየር ላይ ትርኢት እንደሚካሔድ በዚህም የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እንደሚሳተፍ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!