በአማራ ክልል የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሠብሠብ 26 ኮምባይነሮች ሥራ ላይ እንደሚገኙ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

28

ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የጥራት መጓደል እና የምርት ብክነት መከላከል እንደሚገባ ግብርና ቢሮ አሳስቧል፡፡

አርሶ አደር እውነቱ ተረፈ የባሶ ሊበን ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር እውነቱ አምስት ገመድ መሬት ላይ ስንዴ ዘርተው ነበር፡፡

ወረዳው ላይ ኮምባይነር በመኖሩ ሰብላቸውን በአንድ ቀን አስወቅተዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን በመጠቀማቸው በአንድ ወር ተሰብስቦ የማይጠናቀቀው ሰብላችን በአንድ ቀን በመሠብሰቡ ከብዙ ጉዳት ታድጎናል ይላሉ፡፡

ከጉልበታቸው እና ከገንዘባቸው በተጨማሪ በሰብል ሥብሰባ ወቅት ሊከሰት ከሚችለው ብክነትም ታድገዋል፡፡

አርሶ አደር እውነቱ የአካባባው አርሶ አደሮችም ልክ እንደእሳቸው ሁሉ እድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በባሶ ሊበን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ሙሉቀን ዓለሙ በወረዳው 20 ሺህ 394 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁንም ከ10 ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት በእጅ፣ 7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በኮምባይነር መወቃቱን ተናግረዋል፡፡

ከ12 ሺህ 890 በላይ ሰዎች ምርታቸውን በኮምባይነር አስወቅተዋል፤ በዚህም 273 ሺህ ኩንታል ምርትም ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡ በወረዳው በግለሰቦች 2፣ በዩኔኖች 3፣ ከሌሎች አካባቢዎች 4 በድምሩ ዘጠኝ ኮምባይነሮች አገልግሎት እየሠጡ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

በወረዳው በአጠቃላይ 51 ሺህ 360 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ ነበር፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ 44 ሺህ 840 ሄክታር መሬት ሰብል መሠብሰቡንም ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በክልሉ በዘር ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ሰብል መሠብሰቡን ተናግረዋል፡፡

አቶ አግደው በክልሉ 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑንም አንስተዋል፡፡ ምርታቸውን ከ50 በመቶ በላይ ከሠበሰቡ ዞኖች መካከል ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡

በኮምባይነር 3 ሺህ 330 ሄክታር መሬት ተሠብስቧል፡፡ በትሬሸር 249 ሺህ 55 ሄክታር መሬት መሠብሰቡንም ገልጸዋል፡፡

ከተሠበሰቡ ሰብሎች መካካል ስንዴን ጨምሮ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ በቆሎ እና መሰል ሰብሎች መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ 26 ኮምባይነሮች የምርት መሠብሰቡን ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት አቶ አግደው 15 ኮምባይነሮች ምርጥ ዘር እየሠበሰቡ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ኮምባይነሮች በዩኔኖች፣ በግል ባለሀብቶች፣ በምርጥ ዘር አቅራቢ ኢንተርፕራይዞች፣ በኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን እና በአግሪ ሴፍቲ የቀረቡ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 267 አነስተኛ ትሬሸሮች በክልል አገልግሎት እየሠጡ ነው ብለዋል፡፡

አቶ አግደው ባለፈው ዓመት 43 የሚደርሱ ኮምባይነሮች በክልሉ ላይ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ጠቅሰው በዚህ ዓመት ባለው ተጨባጭ ኹኔታ ሁሉንም አካባቢ በኮምባይነር ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች ሳይዘናጉ ሰብላቸውን በወቅቱ በሰው ጉልበት መሠብሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዲኹም በሰው ሠራሽ ችግር ለብክነት እንዳይጋለጥ ምርትን መሠብሰብ ምርጫ ውስጥ የማይገባ ጉዳይ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

አሠባሰቡ ይለያያል ያሉት አቶ አግደው የተወሰነው ወደ ጎተራ ገብቷል፡፡ ቀሪው ደግሞ ማሳ ላይ በአግባቡ ተከምሯል ነው ያሉት፡፡

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሠብሰብ ሊከሰት የሚችለውን የጥራት መጓደል እና የምርት ብክነት መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በውኃ ዋና ስፖርት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች፡፡
Next articleየአየር ኀይል የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየት ያለመ የአየር ኀይል ቀን እየተከበረ ነው።