
ባሕር ዳር: ሕዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ያለንበት ዘመን በቴክኖሎጂ ምጥቀት ሽፋንና በተግባቦት ዝማኔ ያልተጣጣመ እርምጃ የድህረ እውነት የመረጃ አብዮት የእውነትን መሰረት የመሸፋፈን፣ የግነት መረጃዎችን የመርጨት፣ የነጭ ውሸት ፍብረካና ስርጭትንም በጉላት ፈጥሯል።
የዚህ የድህረ እውነት የመረጃ ጡዘት ፈተና በከረረ የፅንፈኛነት አቋም ታጅቦ ሲቀጥል ደግሞ ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል። እንደ ሕዝብ ያለንበት አሁናዊ ሁኔታ ይህንኑ የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያችን የአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች የምዕራባዊያን ፍላጎት መሙያ ፍሪዳነት የቋጨች የነፃነት ቀንዲል የሆነችው ስለልጆቿ አንድነትና ትብብር፣ ስለመሪዎችና ኅብረተሰብ መደማመጥ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ለሀገሬ ከሚል ቀናዒ ስሜት ነበር።
ኢትዮጵያዊያንን ገጥሞ ድል ማድረግ የማይታሰብ መሆኑን የገመገሙ ኀይሎች በቀየሱት ኢትዮጵያዊያንን አጋጥሞ የማሳነስና ማሸነፍ ቀመር ከተቃኙ ቆይተዋል።
ለዚህ ጥንስስ ከተዘረጉ ወጥመዶች አንዱ በሆነው የፅንፈኛነት ክር ላይ የተንጠለጠሉ፣ አንዱን ነጥሎ በመያዝ በማጓተትና በማፈላቀቅ የተናጠልና ተገፋፊ ጉዞን አስከትሏል። ይህም የፅንፍ እይታና እንቅስቃሴ በርካታ ቀውሶችን እያስከተለ ማኅበረሰብና ትውልድን ለብዙ መከራና ውድቀት አስከትሏል።
በአማራ ክልል ደረጃም የአማራን ጥያቄዎች አጣቅሶ፣ የበደሎችን ሁኔታ ተንተርሶ መልሶ ራሱን የአማራን ሕዝብ ለሰቀቀንና ቀውስ ዳርጎት ቆይቷል። የፅንፈኛነትና የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭትም ፈተናዎቻችን ሆነው እንደቀጠሉ ናቸው።
በመሆኑም በስሜት ኮርኳሪና የውድቀት መሪ የተሳሳቱ መረጃዎች ባለመጠለፍ ሀቅን ከስሩ የመመርመርና የማጣራት አቅምን በማሳደግ እንዲሁም የፅንፈኞችን የሴራ መረብና አካሄድ በመረዳት ራስንና ወገንን ከጥፋት መታደግ ከሁሉም ይጠበቃል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!