
ጅግጅጋ: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሱማሌ ክልል እየተከበረ በሚገኘው የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ላይ የተገኙት የሱማሌ ክልል የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀሰን ቃሲም (ዶ.ር) በዓሉ ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን ቱባ ባሕል በአንድ ላይ አቅርበው የሚያስተዋውቁበት ነው ብለዋል።
በዚህም ባሕላቸውን ለሌላው ከማስተዋወቅ ባሻገር የሚተሳሰሩበት እንደኾነም አስገንዝበዋል። ክልሉ ራሱን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል እንደፈጠረለት ነው ያብራሩት።
የበዓሉ የክብር እንግዳ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ “ያለንን ሀብት በጋራ በማምጣት ኢትዮጵያዊነትን የምናጎላበት ቀን ነው” ብለዋል። በልዩነት ውስጥ የሚገለጥ አንድነት እንዳለም የሚታይበት አጋጣሚ እንደኾነ ገልጸዋል። በዓሉ ልዩነት ሳይኾን ኅብረ ብሔራዊነት እንዳለ የሚታይበት እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ይህ ውበት እንዲወጣ በይቅርታ፣ በመተባበር እና ሀገር በመገንባት ለልጆች እንድትሸጋገር ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
ኅብረ ብሔራዊነት ጎልቶ እንዲታይ ይቅርታን በማስቀደም ሁሉም ለሀገር እንዲሠራ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በበዓሉ ሁሉም ተሳታፊዎች ይዘውት የመጡትን እና በየአካባቢያቸው ዕለት ዕለት የሚጠቀሙባቸውን መገልገያዎች፣ ምግቦች እና ባሕላዊ ጭፈራዎቻቸውን አስጎብኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አብነት እስከዚያ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!