
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ጥቂት ወራት በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እና የጸጥታ ችግር ምክንያት ዘርፈ ብዙ ጉዳት ደርሷል።
ክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ከደረሰበት ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ቆመዋል፤ መሠረተ ልማት ወድሟል እንዲሁም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በበርካታ አካባቢዎች የመንግሥት አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቷል።
የክልሉን ወቅታዊ ሰላም በሚመለከት በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።
ክልሉ ከአራት እና አምስት ወራት በፊት የህልውና ፈተና ተጋርጦበት እንደነበር ያነሱት አቶ ይርጋ “አሁን በመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የፀጥታ ኀይሎች ላይ ጫና መፍጠር የሚችል የታጠቀ ቡድን የለም”ብለዋል። ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም ሕዝቡ ከክልሉ የፀጥታ መዋቅር እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በትብብር ሠርቷል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት በአንድ እጁ ሰላም እያስከበረ በሌላ እጁ በበርካታ አካባቢዎች ሕዝባዊ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱንም አቶ ይርጋ አንስተዋል።
በበርካታ አካባቢዎች በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ችግር ፈጣሪዎቹን ከሕዝብ መነጠል ተችሏል ነው ያሉት። በውይይቶቹ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ሁለት ጥያቄዎች አሉ ያሉት አቶ ይርጋ ሕግ እንዲከበርለት እና የመንግሥት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገባ ጠይቆናል ነው ያሉት።
በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት ከህልውና ስጋት ቢላቀቅም ዘላቂ ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል ነው ያሉት። ይህንንም ለማድረግ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ተላልፏል እድሉን የተጠቀሙም ወደ ሰላማዊ ሕይዎት እየተመለሱ ነው ብለዋል።
አቶ ይርጋ አሁንም በሽምቅ ተንጠባጥበው እና ተበትነው ሕዝብ የሚያንገላቱ እና ገጽታ ለማበላሸት የሚጥሩ እንዳሉ አንስተው ሕግ የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!