
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሬው ሰው “ማስተማርያም አታድርገኝ፤ መማርያም አትንሳኝ” ይላል፡፡ ብልህ ከጎረቤቱ ሲማር ሞኝ ደግሞ በራሱ ላይ እስኪደርስበት ይጠብቃልና፡፡
በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ጥንት ሳይኾን ትናንት፣ ከትናንትም ዛሬ፣ ከዛሬም አሁን ማስተማሪያ የሚኾኑ አያሌ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ ከማስተማሪያዎች የተማረ ግን ያለ አይመስልም፡፡ ትናንት ያሳሳተው መንገድ ዛሬም የሚደግመው፣ ትናንት የመታው እንቅፋት ዛሬም የሚመታው፣ ትናንት የወጋው እሾህ ዛሬም የሚወጋው፣ ትናንት የወሰደው የውኃ ሙላት ዛሬም የሚወስደው እየበዛ ነው፡፡
በዚህ ዘመን በልቶ ማደር ቅንጦት፣ ሰላም ውሎ መግባት ቅብጠት የኾነባቸው እልፍ አዕላፍ ወገኖች አሉ፡፡ ቁርስ በልተው ምሳ አይደግሙም፣ ለእራት አይሰባሰቡም፡፡ ርሀብ እየገረፋቸው፣ ማጣት እየኮሰኮሳቸው፣ ችግር እየመረራቸው ዝም ብለው የሚኖሩት እልፎች ናቸው፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንዲሉ በርሀብ ላይ ግጭት፣ እርዛት ላይ ወጥቶ የመግባት ሥጋት ሲደቀን ይስተዋላል፡፡ ርሀብን እያስታመሙ በሰላም መተኛትም ባልከፋ ነበር፡፡ ርሀብ አንጀታቸውን አጥፏቸው፤ የሰላም ስጋት ደግሞ አላስተኛ ይላቸዋል፡፡ አበው “ ሰላም ካለ ውኃም እራት ነው” ይላሉ፡፡ ሰላም ሲጠፋ ወንዝ ወርዶ ውኃ ቀድቶ መጠጣትም ቅንጦት ይኾናል። በዚህ ሰሞን ዛሬንስ እንዲህ አለፍን፣ ዛሬንስ እንዲህ ዋልን ነገስ ምን እንኾን? እያለ የሚሰጋው ብዙ ነው፡፡ ጥል
የሰላምን ቦታ ተክቶባቸው ብዙዎች ተቸግረዋል፡፡ ዛሬን ጎርሰው ነገስ ምን እንበላለን? የዛሬን ለብሰው ነገስ ምን እንለብስ ይኾን? ዛሬስ ይኹን ነገ ልጆቻችን እንጀራ ሲሉን ምን እንመልስ? እያሉ የሚጨነቁት ብዙዎች ናቸው፡፡
ግጭት ብዙዎችን ሥራ አጥ አድርጓቸዋል፡፡ ጉሮሯዋቸውን ዘግቶባቸዋል፤ ሠርተው የሚገቡበትን፣ ትዳር የሚመሩበትን፣ ልጆች የሚያሳድጉበትን ተቋም አሳጥቷቸዋል፡፡ ተቋሞቻቸው ሲያጡ እነርሱም የዕለት ጉርሳቸው፣ የዓመት ልብሳቸውን፣ ክፉ በጎውን ማሳለፊያ ቤታቸውን አጥተዋል፡፡
ከክረምት ወቅት ጀምሮ በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት ችግር ምክንያት የብዙዎች ሕይወት ተናግቷል፡፡ ከንብረት ውድመት አልፎ ውድ የኾነው የሰዎች ሕይወትም አልፏል፡፡ ከዛሬም አሁን የሚራቡ እና የሚጠሙ፣ ታመው ሕክምና የማይሄዱ፤ ገበያ ገብይተው የማይመለሱ ብዙዎች ናቸው፡፡
በዚህ የግጭት ወቅት ከወደሙ ተቋማት መካከል የጣና ፍሎራ የአበባ ምርት አንደኛው ነው፡፡ ይህ የአበባ ምርት ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠረ፣ ለሀገርም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች የነበረው ነው ይላሉ ሠራተኞቹ፡፡ ታዲያ ከባድ ውድመት ከደረሰበት ወዲህ ብዙዎች ሥራ አጥ ኾነዋል፡፡ ያሉትም ከዛሬ ነገ እንሰናበት ይኾን እያሉ በስጋት ውስጥ ናቸው፡፡
በጣና ፍሎራ አበባ ምርት የመስኖ ተቆጣጠሪ መኳንንት ወርቁ ቤቴ የሚሉት ጣና ፍሎራ ከወደመ ወዲህ በስጋት ሕይወትን እየገፉ መኾናቸውን ነግረውናል፡፡ ጣና ፍሎራ ከጉዳቱ ማገገም እየቻለ አይደለም፤ በፊት ከደረሰበት ጉዳት ለመውጣት ሢሰራ ቢቆይም በቅርብ ጊዜ ደግሞ ሌላ ሥርቆት ተፈጽሞበታል ነው ያሉ፡፡ የአበባ ምርቱ ከመውደሙ ማግሥት ሁለት ትራንስፎርመሮችን ተሰርቋል፡፡
የትራንስፎርመሮቹ መዘረፍ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ኾኖበታል፡፡ ከወደቀበት ለመነሳት የሚፍጨረጨረውን የአበባ ምርት ሌላ እክል ኾኖበታል። በጣና ፍሎራ ተቀጥረው ትዳር ሲመሩ፣ ልጆችም ሲያሳድጉ የነበሩ ሠራተኞች አሁን ላይ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ አቶ መኳንንት እድለኛ ኾነው በሥራ ገበታቸው ላይ ተገኙ እንጂ ሌሎች ግን ሥራ አጥተው፣ በችግር ሰንሰለት ታስረዋል፡፡
ጣና ፍሎራ በደረሰበት ውድመት ምክንያት ሥራ ያጡ ወገኖች የሌሎች ጥገኛ መኾናቸውንም ነግረውናል፡፡ በደረሰው ያልታሰበ ችግር ለልመና የወጡም አሉ፡፡ እኛም ስጋት ላይ ነን፣ ነገስ ምን እንኾን ይኾን? በዚህ ከቀጠለ የእኛ እጣ ፋንታስ ምን ሊኾን ይችላል? እያልን እንጨነቃለን፣ የአበባ ምርቱን ወደ ቀደመ ቁመናው ለመመለስ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ያስፈልጋሉ፣ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ጣና ፍሎራ በዚህ ከቀጠለ የእኛም እጣ ፋንታ እንደሌሎቹ ይኾናል ነው ያሉት የችግሩን ክብደት እና ሥጋታቸውን ሲናገሩ፡፡
በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ጣና ፍሎራ ወደ ነበረበት ካልተመለሰ የእኛ ነገ አደጋ ላይ ነው፤ ወደ ቀድሞው ከተመለሰ ሠራተኞቹ ይመለሳሉ ነው ያሉት፡፡ “ዋስ ያልከው ድርጅት ባልጠበቅኸው መንገድ ሲወድም ስሜቱ ከባድ ነው፤ ስነ ልቡና ይጎዳል፤ የጣና ፍሎራ እዚህ ለመድረስ ብዙ ደረጃዎችን አልፏል፤ በቀላል ነገር የሚጠገን አይደለም፤ ድርጅቱ ወድሞ ሲታይ ከባድ ስሜት አለው፡፡ በወደመ ጊዜ አልቅሰናል፤ አሁንም ስጋት አለኝ፤ በዚህ የሚቀጥል ከኾነ የእኔስ የወደፊት ተስፋዬ ምንድን ነው ? ጓደኞቻችን ተበታትነዋል፤ ልጆች ያሏቸው ማሳደጊያ አጥተዋል፤ ሰላም ከሌለ ውሎ መግባት ሠርቶ መብላት አይቻልም” ነው የሚሉት፡፡
የሰላም መጥፋት ብዙ ነገርን ያሳጣል፣ ሁሉም ሰላምን መምረጥ እና ማስቀድ አለበትም ይላሉ፡፡ ሰላም ካለ ልጆች ያድጋሉ፣ ጥያቄዎች ይመለሳሉ፣ ሳይታሰብ የሚሞቱትም ይተርፋሉ ነው የሚሉት፡፡
በጣና ፍሎራ የጄኔሬተር ኦፕሬተርሩ ካሳሁን ዓለማየሁ ቤቴ የሚሉት ተቋም በመውደሙ ስለነገ አብዝተው የሚጨነቁ ኾነዋል፡፡ ጣና ፍሎራ ለእኛ ብቻ ሳይኾን ለሀገርም ትልቅ ሃብት ነበር፤ የእኛ ኹሉም ነገራችን ነው ይላሉ፡፡ ተቋሙን እንደ ቀድሞው ለመመለስ አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡
“ሥራ ያጡ ልጆች አሉ፣ እኛም አሁን ሥጋት ላይ ነን” ነው ያሉት፡፡ በየአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ስለ ሰላም መሥራት ይገባል፤ ሁሉም ለሰላም ማዋጣት አለበት፤ ከዚህ መማር ካልተቻለ ግን የከፋ ችግር ይመጣብናልም ብለዋል፡፡
በጣና ፍሎራ የምርት ክፍል ባለሙያ ቤተልሔም ይስማው ጣና ፍሎራ ለብዙዎች ብዙ ነገር የሰጠ አሁን ደግሞ ብዙ ነገር ያጣ ነው ይሉታል፡፡ በምጣኔ ሃብት እና በስነ ልቡና ከፍተኛ ጫና ደርሶብናል፤ እኛ እድለኞች ኾነን አለመበተናችን እንጂ ችግሩ ከባድ ነበር ብለዋል። “አሁንም ስጋት ላይ ነን፤ አስቸጋሪ ነው፤ ተቋሙን መልሶ ለማቋቋም በሚል የተወሰኑ ሠራተኞች ተጠርተው ነበር፤ ነገር ግን ባለው ሥርቆት አሁንም ስጋት ላይ ነን” ነው ያሉን፡፡ ሁሉም ልጆቹን መምከር፣ ለጥፋት የሚነሱትም መገሰጽ አለበት፤ ካልኾነ ግን የከፋ ችግር ላይ እንወድቃለን ይላሉ፡፡
በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኢንቨስትምንት ፕሮጀክቶች ድጋፍ እና ክትትል ባለሙያ ተመስገን በለው በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአበባ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ፕሮጀክቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ከፍተኛ የኾነ የውጭ ምንዛሬ ሲያስገኝ የነበረው እና ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል የፈጠረው የጣና ፍሎራ ፕሮጀክት ከፍተኛ ውድመት ደርሶበታል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ቢሮው የጉዳት መጠኑን በማየት መፍትሔ እንዲሰጠው በየደረጃው ለሚገኙ አካላት አቅርቧል፡፡
ወደፊት በመንግሥት ድጋፍ እና በራሱ ሊያንሰራራበት የሚችልበትን መንገድ እንዲያመቻቹ እያደረጉ መኾኑንም ተናግረዋል። የክልሉ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የአበባ ምርቶችን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ መጠየቃቸውንም አንስተዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው እየተነጋገሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ እና ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመኾናቸው እነርሱን ማስቆም ለክልሉ ከፍተኛ ኪሠራ ነው ይላሉ፡፡ በዘላቂነት ለማሠራት ከማኅበረሰቡ ጋር መወያዬት፣ ችግሩን መለየት፣ የጋራ መፍትሔ ማበጀት እና ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፖሊስ ማደራጀት ከተቻለ የአበባ ምርቶቹ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ቀጣይነት ይኖራቸዋል ነው የሚሉት፡፡
ሰላም ከጠፋ አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ፣ በአጠቃላይ እኛ ነገ ምን እንኾን? ምን ይገጥመን ይኾን? ለመሥራት አይደለም ለመለመንም ሰላም እና ሰላማዊ ሕዝብ ያሥፈልጋልና፡፡ ነገስ ምን እንኾን? የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
ችግሮቻችንን በአጭሩ ቀርፈን ሰላምን ካልሰፈነ ነገስ ምን እንኾን ይሆን?
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!