በአማራ ክልል በ14 ከተሞች የመሬት ምዝገባ (ካዳሥተር) ሥራ እየተሠራ መኾኑን መሬት ቢሮ ገለጸ።

103

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መሬት ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ዋነኛው ሃብት ነው።

መሬት የእድገት ዋነኛ የምጣኔ ሃብታዊ ምንጭ እንደመኾኑ ለብልሹ አሠራርም የተጋለጠ እና የመልካም አሥተዳደር ችግር መኾኑን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ዳይሬክተር ቢኒያም መጣልኝ ነግረውናል።
በተለይም በከተሞች የሚገኘው የመሬት አያያዝ

ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጅ የታገዘ ባለመኾኑ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ይበልጥ እንደሚስተዋል ነው ዳይሬክተሩ ያነሱት።

በከተሞች ከመሬት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ሕገ ወጥነት ለመከላከል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ከሚገኙ 683 ከተሞች ውስጥ በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ታቦር፣ በደብረ ብርሃን፣ በደብረ ማርቆስ፣ በፍኖተ ሰላም፣ በቡሬ፣ በእንጅባራ፣ በደባርቅ፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በላሊበላ፣ በወልድያ እና በከሚሴ ከተሞች የካዳስተር ሥራ እየተሠራ ነው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በ14ቱ ከተሞች ከሚገኘው 718 ሺህ ይዞታ ውስጥ 74 ሺህ 309 በሰነድ እና በመስክ ተረጋግጧል። ከዚህ ውስጥ 30 ሺህ 360 ይዞታዎች በዘመናዊ መንገድ ተመዝግበው የመብት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ለ26 ሺህ 834 ይዞታ ካርታ ተሰጥቷል።

በከተሞች የካዳስተር ሥራ በመተግበሩ ግብር የማይከፈልበት የባከነ ቦታ መገኘቱ ተገልጿል። ይህ ደግሞ የመንግሥት ገቢ እንዲጨምር አድርጓል። የመንገድ የፕላን ጥሰቶችን የማስተካከል ሥራም ተሠርቷል።

ግለሰቦች በካርታቸው ብድር ተበድረው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ እድል ፈጥሯል። የድንበር ግጭትን ፈትቷል። ሀሰተኛ ካርታ የተሠራላቸው ቦታዎችም ተገኝተዋል።

ቢሮው የከተማ መሬትን የመረጃ ሥርዓት የማዘመን ሥራ ቢሠራም በበጀት እና በግብዓት አቅርቦት ችግር በተቀመጠው እቅድ መሠረት ማከናወን አለመቻሉ ተነስቷል። በከተሞች የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ትኩረት አለመሥጠት፣ ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ እና የመሬት ቢሮ ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር ችግሮች እንዳሉም ተነስቷል።

ሰነድ አልባ እና ሕገ ወጥ ይዞታዎች ሥርዓት አለመያዝ፣ መሬትን አረጋግጦ በመመዝገብ ለመሬት ቢሮ የሚያስረክብ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶች አለመቋቋም ሌሎች ችግሮች መኾናቸው ተነስቷል። ከዚህም ባለፈ በየአካባቢው የሚገኙ ቁርጥራጭ መሬቶችን እና በግለሰቦች በትርፍ የተያዙ ቦታዎችን ምላሽ የሚሰጥ የአፈጻጸም መመሪያ ባለመውጣቱ የመሬት ሥርዓቱን ባለቤት ሰጥቶ ለመመዝገብ አስቸግሯል ብለዋል።

ከተሞች በሚካሄደው የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ በበጀት እና የሰው ኀይል በማሟላት እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢንዱስትሪዎች ገበያ፣ ካፒታል፣ ብቁ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰላምም መሠረታዊ ጉዳይ ነው” የሰላም ሚንስትር ብናልፍ አንዷለም
Next articleየንግድ ትርዒት እና ባዛር በጅግጅጋ ከተማ ተከፈተ።