“ደራሽ ፈላጊ ወገኖች፤ በማጣት የተዘረጉ እጆች”

47

ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለወትሮው “ሞትና ክረምት አይቀረም” እያሉ የሚናገሩት የሀገሬው ሰዎች ክረምት ሲቀር በዘመናቸው አይተዋል። ጉም እየጎተቱ፣ ዶፍ የሚያወርዱት ወርሃ ሰኔ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ያለ ዝናብ አልፈዋል፡፡

ጋራ እና ሸንተረሮቹ ያለ ልምላሜ ከርመዋል፤ ላም እና በሬዎች፣ ፍዬል እና በጎች ለምለም ሣር ሳይቀምሱ ቀርተዋል፤ በክረምት የሚደነፉት ወንዞች ደርቀዋል፤ ከጓሮው እሸት፣ ከግሬራው ወተት እያማረጡ የሚቀምሱት ሕጻናት ከእሸት እና ከወተት ርቀዋል፡፡

በክረምት እና በመኸር ሣር እየቀጠፉ የሚያገሱት በሬዎች፣ ወተት የሚሰጡት ላሞች፣ ለፍሬ የሚበቁት ወይፈን እና ጊደሮች፣ ላም እና ፍየሎች በረሃብ ሞተዋል፡፡ ያሉትም በረሃብ ተወግተው መንቀሳቀስ ተቸግረዋል፡፡

ከሰማይ የምህረት ዝናብ ቀርቶ፣ በርካታ አካባቢዎች በድርቅ አሳልፈዋል፡፡ ድርቅ ባመጣው ዳፋ ሞተዋል፤ ተርበዋል፤ ተሰደዋል፡፡ ሰጪዎች ኾነው ሳለ የሰው እጅ ተመልካቾች ለምኖ አዳሪዎች ኾነዋል፡፡ በስሜን ጎንደር ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ድርቅ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወገኖች የሰው እጅ ተመልካቾች ኾነዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳትም በድርቅ ምክንያት አልቀዋል፡፡

ድርቁ ባስከተለው ችግር ብዙዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ ነብሳቸውን ለማትረፍ ከቀያቸው ርቀዋል፡፡ ከቀያቸው መራቅ የማይችሉት፣ አቅመ ደካሞች ደግሞ በሩቅ ኾነው ድረሱልን እያሉ ነው፡፡ በጉዳታቸው እና በጥሪያቸው ልክ ግን የደረሰ የለም፡፡

የደባርቅ ዪኒቨርሲቲ በስሜን ጎንደር ዞን የደረሰውን ድርቅ በተመለከተ ጥናት አድርጓል፡፡ በጥናቱም ዘርፈ ብዙ ችግሮች መከሰታቸውን አረጋግጧል፡፡ በርብርብ መደገፍ እና ከችግራቸው ማውጣት ካልተቻለ በርካታ ወገኖች ሊታጡ፣ ያለ ሀብት እና ንብረት ሊቀሩ እንደሚችሉም ይፋ አድርጓል፡፡

በደባርቅ ዪኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር እና የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አምሳሉ ተበጀ ጥልቅ ጥናት ቢጠይቅም የድርቁ መነሻ ምክንያት የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ ጉድለት ያመጣው እንደሚኾን አመለካች ነገር አለ ይላሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የዓለም ሙቀት መጨመር ለብዙዎች ስጋት ኾኗልና፡፡

በጥናቱ እንደተመለካተው በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት፣ በየዳ እና ጃናሞራ በተሰኙ አካባቢዎች ሰፊ ድርቅ ተከስቷል፡፡ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከ16 ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ ተጎድቷል፡፡ 219 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ቀንሷል፤ ወይም ቀርቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ107 ሺህ በላይ ወገኖች ተጎድተዋል፡፡ 36 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል፡፡ ከ72 ሺህ በላይ አንስሳትም ሞተዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የእንሳሰት መኖ እና በሰብል ተረፈ ምርትም ወድሟል፡፡

በመኖ እና በሰብል ተረፈ ምርት ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ከ725 ሺህ ቶን በላይ የመኖ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ በተፈጠረው የመኖ ክፍተት ደግሞ ከ371 ሺህ በላይ እንስሳት ለመኖ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ በረሃቡ ምክንያት የእንስሳት በሽታም ተከስቷል፡፡

ድርቅ ባስከተለው ጉዳት እና በተፈጠረው ርሃብ 14 ሺህ 847 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውም በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል አልቻሉም፡፡ በተፈጠረው ከባድ ድርቅ ወላጆቻቸው ልጆቻቸው የሚመግቡበት አቅም ስላጠራቸው ነው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑት፡፡

ከወላጆቻቸው ርቀው ተከራይተው የሚማሩ ተማሪዎችም ትምህርት ለማቋረጥ ተገድደዋል፡፡ በድርቅ ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የተሰደዱ ወገኖች በመኖራቸው ጥናት በሚካሄድበት ወቅት ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች ነበሩ ነው የተባለው፡፡

የሚባላ እና የሚጠጣ ለመምህራን ጭምር ችግር መኾኑም በጥናቱ ተመላክተዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ እንደገለጹት የእንስሳት ሞት ከፍተኛ መኾን ወደ ፊት በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ነው ያሉት፡፡ እንስሳት ከሌሉ ወደፊትም ማረስ አይቻልም፤ ማረስ ካልተቻለ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ይመጣል፡፡ የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ እንስሳትን ማትረፍ ካልተቻለ በኢትዮጵያ ታሪክ ክፉ ቀን ተብሎ የተመዘገበው ሊመጣ እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

በ1880ዎቹ ገደማ በኢትዮጵያ ታላቅ ርሃብ እና በሽታ ተነስቶ ሰውም ከብትም በዚሁ በሽታ እና ርሀብ ግማሹ የሚሞትበት፣ ግማሹ የሚሰቃይበት ክፉ ጊዜ ነበር በማለት ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጽፈዋል፡፡ በዚህ ዘመን እንስሳት ከማለቃቸው የተነሳ የሚታረስ በሬ ጠፍቶ ሰው ሁሉ እንዲቆፍር ተገድዶ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢም የእንስሳት ሞት የከፋ በመኾኑ በአስቸኳይ መደገፍ ካልተቻለ ክፉ ቀን የሚባለው ሊደርስባቸው ይቻላል የሚሉት፡፡

ጥናቱ እንዳመለካተው በአጭር ጊዜ መፍትሔ አስቸኳይ የምግብ፣ የመጠጥ እና የእንስሳት መኖ አቅርቦት ያስፈልጋል፡፡ ለተጎዱ ወገኖች መድኃኒት እና ዓልሚ ምግብ በወቅቱ ማዳረስ፣ እንስሳትን መኖ ከማቅረብ ባለፈ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ፤ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ያማካለ ድጋፍ ማቅረብ ይገባል ነው የተባለው፡፡ አቅም ደካሞች እና አረጋውያን ከቀያቸው ተሰደው ነብሳቸው ማትረፍ እንደማይችሉም ተመላክቷል፡፡

ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በትምህርት ቤት ምገባ መጀመር እንደሚያስፈልግም ጥናቱ አመላክቷል፡፡ እንደ ጥናቱ ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ፣ አልባሳት ድጋፍ ማድረግ፣ ተማሪዎችን ወደ አንድ አካባቢ በማሰባሰብ ማስተማር ቢቻል መታደግ ይቻላል፡፡

ደባርቅ ዪኒቨርሲቲ ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያ ሰበዓዊ እርዳታ ከማድረስ ጀምሮ፣ ጥናት በማጥናት እና ሌሎች የሚጠበቁበትን በማድረግ አስተዋጽኦ እያደረገ ነውም ተብሏል፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙ የመፍትሔ እጁን ካልዘረጋ የከፋ ችግር ይገጥማል፤ ወገኖቻችን እናጣቸዋለን ነው ያሉት፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን ለተጎጂዎች የሚደርስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡

የደባርቅ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀጃው ደማሙ (ዶ.ር) ዪኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባለፈ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና በምርምር የሚጠበቅበትን እያደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ በተለይም ለአርሶ አደሮች ጠቃሚ እና ቅርብ የኾኑ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በግብርናው ዘርፍ የተሻሻሉ ዝራያዎችን በማቅረብ ጥሩ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ፣ መኖ በማቅረብ እና ጥናት በማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በጥናቱ አማካኝነት ወገኖች እንዲረዱ ጥናቱን ለሚመለከታቸው አካላት እያቀረቡ ነው፡፡ ደባርቅ ዪኒቨርሲቲ ወገኖችን ለመታደግ በሚኖሩ የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ድጋፍ እያደረኩ ነው ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የሁሉንም አካል ርብርብር እንደሚጠይቅ፣ በሀገር እና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ወገኖች ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡

“ደራሽ ፈላጊ ወገኖች፤ በማጣት የተዘረጉ እጆች” እዚህ አካባቢ አሉ እርስዎ ለእነዚህ ወገኖች ምን ሊያደርጉ አስበው ይኾን?

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ120 ሺህ በላይ የኾኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዲያገኙ ማድረጉን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
Next article“ኢንዱስትሪዎች ገበያ፣ ካፒታል፣ ብቁ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰላምም መሠረታዊ ጉዳይ ነው” የሰላም ሚንስትር ብናልፍ አንዷለም