
ባሕር ዳር: ኅዳር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ከ120 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዲያገኙ መደረጉን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የውጭ ሀገር ሥራን አማራጭ ለሚያደርጉ ዜጎች መንግሥት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሥምምነት በመፈራረም በሕጋዊ መንገድ ተሰማርተው የሚሠሩበትን ምቹ ኹኔታ እየፈጠረ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሊባኖስ፣ ጆርዳን፣ ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ውል በመዋዋል ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሔደው እንዲሠሩ እየተደረገ ይገኛል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዜጎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት እድል መኾኑን ገልጸዋል።
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ለሚወስዱ ዜጎች ብቻ ተብለው በተለዩ 94 የሥልጠና ማዕከላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የቋንቋ ችሎታቸውን የሚያጎለብቱበት፣ ገንዘባቸውን በአግባቡ የሚያስተዳድሩበት፣ ስለሚሄዱባቸው ሀገራት በቂ ግንዛቤ የሚይዙበት እና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ ሥልጠና መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዜጎችን የውጭ ሀገር ሥራ የመሰማራት ፍላጎት በሕጋዊ መንገድ ለማሳካት ከተለዩ ሀገራት ጋር በመነጋገር እና ሥምምነት በመፈራረም መዳረሻዎቿን እያሰፋች መኾኑንም ገልጸዋል።
የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር ለማብዛት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ ሀገራት የሥራ ፍላጎቶች እየመጡ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የመዳረሻ ሀገራትን ከማሥፋት በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ አሠራሮችን በማዘመን በወር እስከ 38 ሺህ ዜጎችን መላክ የሚቻልበት አሠራር ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ኢዜአ እንደዘገበው ሚኒስትሯ ከጀርመን የግል ኩባንያዎች ጋር በመነጋገርም የውጭ የሥራ ሥምሪት መሥጠታቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!