
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኦስትሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ያደረጉት ቆይታ እና በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ስኬታማ እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሣምንት በሦስቱ ሀገራት የነበራቸውን ቆይታ በማስመልከት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኀላፊ ቢልለኔ ስዩም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) በኦስትሪያ የነበራቸው ቆይታ እና በቼክ ሪፐብሊክ ጉብኝታቸውም የነበሯቸው ውይይቶች ስኬታማ እንደነበሩ ገልጸዋል።
ቼክ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በመከላከያ አቅም ግንባታ እና ሌሎች መስኮች በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው ኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ያዘጋጀችውን አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ /ፓቪሊዮን/ የሀገራት መሪዎች፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች እና ሌሎችም በመጎብኘት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ዓለም ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዩ ሀገራት በጥሩ ተሞክሮነት የተወሰደ መኾኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ቆይታ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውንም ኅላፊዋ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!