“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ሀገራት የነበራቸው ጉብኝት እና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብር እና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ ነው” ዶክተር ለገሰ ቱሉ

30

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተለያዩ ሀገራት የነበራቸው ጉብኝት እና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ መኾኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባለፈው ሣምንት በኦስትሪያ እና በቼክ ሪፐብሊክ ያደረጉት ቆይታ እና በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የነበራቸውን ቆይታ በማስመልከት የመንግሥት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው በኦስትሪያ የቪየና የመንግሥታቱ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባዔ፣ በዱባይ 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ ተሳትፎ እንዲሁም በቼክ ሪፐብሊክ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

አካታች እና ዘላቂ ኢንዱስትሪ ልማት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል በመከረው በቪየናው የኢንዱስትሪ ልማት ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት የዘርፉ ስኬታማ ልምዶች የቀረቡበት መኾኑን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በመዋቅራዊ እና ሴክተር ማሻሻዎች ላይ አመርቂ ውጤቶች ማቅረቧን እንዲሁም በተቀናጀ አግሮ ኢንደስትሪን ጨምሮ በርካታ ተሞክሮዎቿን አቅርባ አድናቆት የተቸረችበት እንደሆነም አንስተዋል።

ከ140 ሀገራት መሪዎች እና ከ90 ሺህ በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ በተካሄደው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ ተሞክሮ መቅረቡን ገልጸዋል።
የሀገራት መሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከተናጠላዊ ይልቅ የተቀናጀ የመፍትሄ እርምጃ ውጤታማ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ንብረት ቀውስ ታዳጊ ሀገራት ለሚደረስባቸው ጉዳት የበለጸጉ ሀገራት እንደ ችሮታ ሳይሆን እንደ ግዴታ ወስደው መደገፍ እንደሚገባቸውም በመድረኩ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ቱርፋት፣ በስንዴ ምርታማነት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የተገኙ አምርቂ ውጤቶች በዘርፉ ተግባራዊ እርምጃን አስቀድማ እያከናወነች መኾኑን ማውሳታቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን መሰል ስኬታማ ሥራ የሠሩ ሀገራት ሊደገፉ እንደሚገባ መናገራቸውን ዶክተር ለገሰ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ በዱባይ በመካነ ርዕይ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኘቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎብኝት እና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ እንደነበር አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው የሥራ ጉብኝት ከሀገሪቱ መሪ ጋር በኢትዮ-ቼክ የሁለትዮሽ ታሪካዊና ነባር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መምከራቸውን አንስተዋል።

ከመሪዎች በተጨማሪም ከቼክ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች ጋር ውይይቶች ስለማድረጋቸው አስታውሰው፤ በተለያዩ ታሪካዊ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፤ ጉብኝታቸው የተሳካ ነበር ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በድርቅ እና በአንበጣ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለመስኖ ልማት ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር እየተሰራጨ ነው” ግብርና ቢሮ
Next article“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኦስትሪያና ቼክ ሪፐብሊክ ያደረጉት ቆይታ እንዲሁም በኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ስኬታማ ነበር” ቢልለኔ ስዩም