
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር መላሽ ዓለሙ ይባላሉ። በጃናሞራ ወረዳ የአይጠጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ በርካታ ንብረቴን አሳጥቶኛል ይላሉ። ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንም ተናግረዋል።
አርሶ አደር መላሽ እንዳሉት በድርቁ ምክንያት 70 ኩንታል የሚገመት ሰብል ሙሉ በሙሉ ወድሞባቸዋል። ከ30 በላይ በጎች ሞተውብኛል ነው ያሉት። በቅሎዎች እና የቤተሰቦቻቸው ሕይዎት መሠረት የኾኑት የእርሻ በሬዎችን ጭምር አጥተዋል። በደጉ ዘመን ለገበያ በማቅረብ ሸማቹን ማኅበረሰብ ሲመግቡ የነበሩት አርሶ አደር አሁን ላይ የ11 ቤተሰቦቻቸውን ሕይዎት ለመታደግ የየአብያተክርስቲያናቱን እና ባለሀብቶችን በር ማንኳኳት ግዴታ ኾኖባቸዋል።
ቁርስ ከተመገቡ ምሳ እና እራት የማይደግሙበት ቀን እንደሚበዛም ነግረውናል። ድርቁ ያስከተለው ጉዳት በቤተሰባቸው በተለይም ደግሞ በልጆች ላይ ከፍተኛ አካላዊ እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳደረሰ ነው የነገሩን።
ከሰብዓዊ ድጋፍ ባለፈ በአካባቢው ለመስኖ ልማት አመች የኾኑ አካባቢዎች እንዲለሙ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በአርሶ አደር መላሽ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለአብነት አነሳን እንጂ በክልሉ በድርቅ በተጎዱ 42 ወረዳዎች የሚገኙ አምራች አርሶ አደሮችም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ አጋጥሟቸዋል።
የጃናሞራ ወረዳ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ ሸጋው ተሰማ እንዳሉት በወረዳው 13 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ ከ57 ሺህ በላይ ሕዝብ ለረሀብ እና ለበሽታ ተጋልጧል። ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ተቋማት እና ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ ቢያደርጉም ካጋጠመው የችግሩ ስፋት አኳያ በቂ አለመኾኑን አንስተዋል።
ተቋማት እና ድርጅቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር በክረምት የታጣውን ምርት በበጋ መስኖ ለማካካስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ወረዳው ካለው ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ በመስኖ የመልማት አቅም 600 ሄክታር መሬት በስንዴ ለማልማት እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 345 ሄክታር መሬት ታርሷል፤ 175 ሄክታር መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል ብለዋል። ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ማኅበረሰቡ ዘር፣ ማዳበሪያም ኾነ ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ አግሮኖሚ ባለሙያ ተሻለ ዓይናለም እንደገለጹት ድርቅ እና አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመስኖ ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል። ባለሙያው እንዳሉት እስከ አሁንም 4 ሺህ 300 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅርብ ዝግጅት ተደርጓል። 4 ሺህ 461 ኩንታል ማዳበሪያም በመሰራጨት ላይ ይገኛል።
በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ማልማት ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይኾን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል። አርሶ አደሮች ሙሉ አቅማቸውን መሥኖ ልማት ላይ እንዲያውሉም ጠይቀዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች እና ኀላፊዎች የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የሚቀርበውን ግብዓትም ፍትሐዊ በኾነ መንገድ እንዲሰራጭ እና ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ክትትል ማድረግ ይገባል
ነው ያሉት።
መንግሥታዊም ኾኑ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦችም ችግር ላጋጠማቸው አካባቢዎች የውኃ መሳቢያ ፓምፖችን፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!