
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ ዕድል እና የልማት አጀንዳዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ ተደራሽ እና አካታች እንዲኾኑ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አሳስቧል።
የምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓቱም ኾነ የሥራ ዕድል ፈጠራው አካል ጉዳተኞችን አካታች አይደለም ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ፍሬስብሐት ዘገየ ገልጸዋል። ”ወጣት እና ሴት አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ግንዛቤ ያልተያዘበት የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው የሚከናወነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ የጤና ተቋማት ሲገነቡም ኾነ አገልግሎት አሰጣጡ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
”ሕገ መንግሥታችን ለአካል ጉዳተኞች የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት በፈቀደ መጠን ድጋፍ እና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ቢደነግግም የሥራ ዕድል ሲፈጠርላቸው አይታይም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ አካል ጉዳተኛውን መርዳት ሳይኾን በገቢ ማስገኛ ሥራ በማሰማራት ለሀገሪቱ አስተዋጾኦ እንዲያበረክት ማስቻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለተግባራዊ ምላሽ ፖለቲካዊ ትርጉም መስጠት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ፍሬስብሐት ”ለአካል ጉዳተኞች ተቋማዊ ውክልና በመስጠት ተቋማዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ” ገልጸዋል።
የጤና፣ የትምህርት እና የፍትሕ ተቋማት ላይ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ስለሌለ መስማት የማይችሉ ወገኖች የሚስተናገዱበት አሠራር አለመኖሩን ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።
“የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ማኅበራዊ ጉዳይ በሚል መጋረጃ ውስጥ ስለተቀመጠ ተቋማዊ ውክልና የለንም፤ ስለኾነም ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት በተቋማዊ ውክልና ቢሠራበት የአካታችነት እና የተደራሽነት ጉዳይ ይቀረፋል” ሲሉ አመላክተዋል።
በኬንያ አካል ጉዳተኞች በምክር ቤቶች የድምጽ ውክልና እና የምልክት ቋንቋን በሥራ ላይ መዋልን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው፦
👉 መንግሥት አካል ጉዳትን እንደ አንድ የተለየ ማኅበረሰብ ልዩ እውቅና ሰጥቶ ወካይ ተቋማዊ ሥርዓት መዘርጋት ይገባዋል።
👉 አካል ጉዳተኞችን በበጀት፣ በቢሮና በቁሳቁስ መደገፍ ያስፈልጋል።
👉 የሕንጻ እና የሥራ ሥምሪት ሕጎች እንዲሻሻሉ ማድረግ ይገባል።
👉 ምሁራን ከአካል ጉዳተኞች አኳያ ጥናትና ምርምር በማድረግ መደገፍ ይጠበቅባቸዋል።
👉 መገናኛ ብዙኃን ስኬታማ የአካል ጉዳተኞችን የሕይዎት ተሞክሮ ለማኅበረሰቡ በማቅረብ እንዲያስተምሩ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!