
“በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ለውጥ ለማድረግ የወጣ መረጃ የለም” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በመስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች መሆኑን ባንኩ ለአሚኮ በላከው መግለጫ አረጋግጧል።
የባንኩ ሙሉ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል፦
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ መግለጫ
የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ በኅዳር 23፣ 2016 እትሙ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት ላይ ተነሥቶ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በመስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች፣ ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በመሆኑም፣ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በተመለከተ የቀረበ ዕቅድ ካለመኖሩም ባሻገር እስከ አራት ሰዓት በፈጀው ውይይት ወቅት በብሔራዊ ባንክ የተነገረ ነገር እንደሌለ ኅብረተሰቡ ተረድቶ፣ ከዚህ ዐይነት አሳሳች መረጃ እንዲጠበቅ፣ የሪፖርተር ጋዜጣም በሚቀጥለው እትሙ ይህንኑ የሐሰት ዘገባ እንዲያርም እየጠየቅን፣ በዚህ አሳሳች ዘገባና አሉባልታ ምክንያት በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ሰው ሠራሽ ጭማሪ ተቀባይነት እንደማይኖረውና ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!