
ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን መግለጫ ሰጥተዋል።
የልማት አጀንዳዎችን ስኬታማ ለማድረግ የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ወሳኝ እንደኾነ የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍሬስብሐት ዘገየ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል 4 ሚሊዮን ሰዎች አካል ጉዳተኛ መኾናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ እነሱን ያላሳተፈ የልማት አጀንዳ ውጤታማ መኾን አይችልም ብለዋል። አካል ጉዳተኞች ሰፊውን ማኅበረሰብ ስለሚሸፍኑ ከድህነት መላቀቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አቶ ፍሬስብሐት የትምህርት ሥርዓቱ አካታች ባለመኾኑ እና ትምህርት ቤቶችም ስለማይመቹ አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት አይመጡም፤ የመጡትም ቢኾኑ አቋራጮቹ እንደሚበዙ ነው የተናገሩት። በክልሉ የትምህርት ዕድል ያገኙት የአካል ጉዳተኞችም ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው ብለዋል።
”አካል ጉዳተኞች ምቹ ኹኔታ ከተፈጠረላቸው በየትኛውም ዘርፍ ላይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ይኾናሉ” ያሉት ፕሬዚዳንቱ የትምህርት እና የጤና ሥርዓቱ ለአካል ጉዳተኞች አሳታፊ፣ አካታችና ተደራሽ እንዲኾን ጠይቀዋል።
አቶ ፍሬስብሐት ”አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በየዓመቱ በዓልን ማክበር ብቻ ሳይኾን ምቹ ኹኔታ መፍጠር ይገባል” በማለት የሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ ለ30 ዓመታት ስለግንዛቤ ፈጠራ ብቻ መሥራት ውጤት እንደማይኾን ነው የገለጹት።
ቀኑ ”ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ለዘላቂ ልማት ትርጉም ያለው ትብብር” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ክዋኔዎች እንደሚከበርም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!