የጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሆስፒታል የካንሰር እና ልብ ህክምና አገልግሎቱን ማሳደግ የሚችል የሕንፃ ግንባታ እያከናወነ አንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

47

አዲስ አበባ፡ ኅዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር በስሩ የሚገኙ ሆስፒታሎች እና የአገልግሎት ተቋማት ማስፋፊያ ሥራዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምከርቤት አባላት እያስጎበኘ ነው።

በጉብኝቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤን ጨምሮ የጤና፣ ማኅበራዊ፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ እና የምከርቤት አባላት ጉብኝት እያካሄዱ ነው።

ለምክር ቤት አባላቱ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ 76 ዓመታትን ያስቆጠረ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ሆስፒታሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱን በማሳደጉ 862 አልጋዎች አሉት ብለዋል።

ባለፈው 2015 ዓ.ም 632 ሺህ ተመላላሽ ታካሚዎችን አገልግሎት መስጠቱን፤ 39 ሺህ አስተኝቶ ማከም እና 21 ሺህ ቀዶ ጥገና ህክምና ማካሄዱን አብራርተዋል።

ሚኒስትሯ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ የማስተማር ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም በቅድመ ምረቃ በሰፔሻሊቲ እና ሰብ-ስፔሻሊቲ አገልግሎት እየሰጠ ነው የሚገኘው።

ይህንን አገልግሎቱን ማሳደግ የሚያስችለውን ሕንፃ ማስፋፊያ በሁለት ቢሊዮን ብር እያካሄደ ሲኾን ሕንፃው ወደ አገልግሎት ሲገባ ተጨማሪ 1ሺህ 67 አልጋዎች እንደሚኖሩትም ተገልጿል።

ማስፋፊያው በዋናነት የካንሰር እና የልብ ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

የሕንፃ ግንባታው 85 በመቶ መድረሱ ተመላክቷል። በሀገሪቱ ባጋጠመው የሲሚንቶ አቅርቦት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መጠናቀቅ ከሚገባው ጊዜ መዘግየቱን ተናግረዋል ።

በመርሐግብሩ የኢትዮጵያ መድኃኒት አገልግሎት፣ የአለርት ሆስፒታል እና የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ ሰጭ አገልግሎት ድርጅት እየተጎበኙ ነው።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላምን እንጅ ግጭት አንፈልግም፤ በግጭትም የሚመጣ ለውጥ የለም” የዱርቤቴ ከተማ ነዋሪዎች
Next article“የልማት አጀንዳዎችን ስኬታማ ለማድረግ የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው” የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን