
ባሕር ዳር: ሕዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎጃም ዞን ዱርቤቴ ከተማ አስተዳድር “አብሮነት ለሰላም፣ ሰላም ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ሐሳብ ሕዝባዊ ውይይት ተካሄዷል፡፡
በውይይቱ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳድር አመራሮች፣ የደቡብ አቸፈር ወረዳ እና የዱርቤቴ ከተማ አስተዳድር አመራሮች ተገኝተዋል።
የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳድር ምክትል ከንቲባ በሪሁን ቢረሳው “ሰላማችንን ሊያደበዝዙና የልማት ጉዟችንን ሊያደናቅፉ የሚችሉ አጋጣሚዎችን በጋራ ልንታገላቸው ይገባል” ብለዋል፡፡
የዱርቤቴ ከተማ አሥተዳድር እና የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪዎች “ሰላምን እንጅ ግጭት አንፈልግም፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንጅ በግጭትም የሚመጣ ለውጥና ውጤት የለም፤ የምንፈልገው አንድ መንግሥትና ሰላም ነው” ብለዋል።
ምክትል ከንቲባው ለዘመናት በፍቅር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት የኖረውን ሕዝብ ዒላማቸው በማድረግ፤ በሕዝብ ጭንብል የራሳቸው የስልጣን ጥምና ጥቅም ለማርካት ሌት ተቀን የሚሠሩ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
ምክንያት እየፈለጉ ግርግር እና ሁከት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ በሕዝብ እና በመሪዎች ላይ በሚዲያ የተዛባና ሐሰተኛ መረጃን በመርጨት የአካባቢው ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲዳከም አስበው የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
መልካም ሥራዎችን ከማበረታታት ይልቅ በማጣጣልና ምክንያቶችን እየፈለጉ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚፈልጉ፣ የሕዝብን ስብዕና ጭምር የሚነኩ አስነዋሪ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ኀይሎች ዛሬም ነገም ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ “ይህን እኩይ ተግባር ሕዝባችን አምርሮ ሊታገለው ይገባል” ብለዋል፡፡
“የከተማችን ዱርቤቴ እና የደቡብ አቸፈር ወረዳ ሰላም እና ሁለንተናዊ ልማት የሚረጋገጠው በዛሬው የጋራ ልፋታችንና ድካማችን ነገን አስበን ስንሠራ ነው” ብለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው ለመከላከያ ሠራዊቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ 304ኛ ኮር የ99ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ኮለኔል ወሰን አበበ “ሠራዊታችን የመስዋዕትነት ጥግን ለሕዝብ እያስተማረ ሰላምን የሚያሰፍን ሕዝባዊ ሠራዊት ነው” ብለዋል።
ኮለኔሉ አክለውም የሁሉም ችግሮች መፍትሔ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ሕዝብ የመፍትሔው አካል መሆኑን መረዳት እንዳለበት ገልጸዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ በለጠ ጥጋቡ የሕዝብ ልጅ ሁኖ ለሕዝብ የሚሠራ ፖሊስን፣ ሚሊሻና ሌሎች የሰላምና ፀጥታ መዋቅር ለሰላም መስፈን ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን አንስተዋል።
የተሻለ ነገን ለማየት ዛሬን መጠቀም እና ማድነቅ ያስፈልጋል ያሉት አቶ በለጠ፤ ሁሉም አካል ከእኔነት ስሜት ወጥቶ ወደ እኛነት ስሜት እና ስሌት ሊገባ ይገባል ብለዋል።
አቶ በለጠ ሰላምና አብሮነትን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት በጋራ በጽኑ መሰረት ላይ መትከል ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ በመሆኑ ጥላቻን በፍቅር ጨለማን በብርሃን መተካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
መረጃው የወረዳው ኮሙኒኬሽን ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!