“የማይቻለው አለመቻል ብቻ ነው” የሕይወት ክሕሎት ሠልጣኞች

52

ባሕር ዳር: ኅዳር 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የፍቅር ማዕድ” በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሥጦታ ሥርዓት ሥልጠና ማዕከል ሲኾን በሕይወት ክህሎት ያሠለጠናቸውን ወጣቶች አስመርቋል።

ማዕከሉ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ቅርንጫፉ ለ21 ቀናት በሕይወት ክሕሎት እና በሰብዕና ግንባታ ያሠለጠናቸውን 65 ወጣቶች ነው ያስመረቀው።

የማዕከሉ ሥራ አሥኪያጅ ታከለ ንጉሴ እንዳሉት ማዕከሉ ታታሪ ወጣት መፍጠር፣ ወጣቶች በሀገር ውስጥ ሠርተው እንዲለወጡ ማድረግ እና በመንግሥት የተቀመጠውን የሥራ ሰዓት (የ8 ሰዓት የሥራ ባሕል) ማሳደግ ላይ ዓላማ አድርጎ እየሠራ ይገኛል። ወጣቶችን ከማሠልጠን ባለፈ በድርጅቱ የሥራ እድል እየፈጠረ ነው።

ድርጅቱ በ2013 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የተቋቋመ ማኅበር መኾኑን ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ 26 የሥራ ዘርፎችን ለመሥራት አቅዷል። ከእነዚህ ውስጥም አሁን ላይ ዲጂታል የዕቁብ ሥርዓት፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ሱፐር ባንክ ኤጀንት እና የአመለካከት ለውጥ ሥልጠና ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በቀጣይ ሌሎች ዘርፎችን ለመተግበር እየተሠራ መኾኑን ሥራ አሥኪያጁ ገልጸዋል። ማዕከሉ አሁን ላይ በሀገሪቱ ለ80 ሺህ ወጣቶች የአመለካከት ሥልጠና በመሥጠት የሥራ እድል ፈጠሯል ነው ያሉት።

በሥልጠናው የተሳተፉ ወጣቶች እንዳሉት የተሰጠው የሕይወት ክህሎት ሥልጠና የይቻላል መንፈስን የሚያጎለብት እና ከጠባቂነት መንፈስ የሚያላቅቅ ነው። “የማይቻለው አለመቻል ብቻ ነው” ያሉት ሠልጣኞች ራስን ለመለወጥ ከመንግሥት የሥራ ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜ በአልባሌ ከማሳለፍ ይልቅ ተጨማሪ ሥራ በመከወን የስኬትን ቁንጮ መቆናጠጥ እንደሚቻል የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ባገናዘበ መንገድ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን አንስተዋል። ወጣቶች “ከአይቻልም” ስሜት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የፍቅር ማዕድ በሀገሪቱ በሚገኙ 16 ከተሞች ቅርንጫፍ ከፍቶ እየሠራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኩር ጋዜጣ ኅዳር 24/2016 ዓ.ም ዕትም
Next article“ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የደርባኑ ብሪክስ ፕላስ ስብሰባ እንደ ሀገር ለሚጠበቅብን ሥራ መሠረት የጣለ ነው” በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ