
ባሕር ዳር: ሕዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንደላማው በወቅተዊ ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ከተማዋ በችግር ውስጥ እንደነበረች አስታውሰዋል።
ከተማዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስባት መኾኗን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጥፋት ፈጥሮ ማለፉንም ገልጸዋል። የተፈጠረው ችግር የከተማዋን ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጉዳቱንም አንስተዋል።
ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተደጋጋሚ የማኅበረሰብ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። በተሠራው የተቀናጀ ሥራ የከተማዋ ሰላም ከቀን ቀን እየተሻሻለ መሔዱን አስታውቀዋል። የተፈጠረው የሰላም እጦት የበለጠ እንዳይባባስ መሠራቱንም ገልጸዋል።
ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም መደበኛ አገልግሎት እንዲሠጡ መደረጉንም ገልጸዋል።
የመንግሥት ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሠጡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል።
ያደሩ የዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መኾናቸውን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በከተማዋ የተደራጁ ከ800 በላይ ማኅበራት የግንባታ ፈቃድ እንዲሠጣቸው መደረጉንም ገልጸዋል። ይሄም ከ21 ሺህ በላይ አባውራ እና እማውራዎችን የቤት ባለቤት የሚያደርግ እና የቆዬ ጥያቄ የፈታ መኾኑን ነው ያነሱት። በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ውጤት ያስገኙ ሥራዎች መሠራታቸውንም አመላክተዋል።
በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የአርሶ አደር የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እየተሠጠ ነው ብለዋል። የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን መሥራታቸውንም ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው ችግር መንስኤ ላይ ለመግባባት እና የችግሮችን መፍቻ ቁልፍ ለማበጀት ተደጋጋሚ ሕዝባዊ ውይይቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ችግሮች ታውቀውና ተለይተው ያደሩ መኾናቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ችግሮችን በውይይት መፍታት አዋጭ እና አትራፊ መኾኑን ገልጸዋል።
በተደረጉ ውይይቶች ከኅብረተሰቡ ጋር ሰላምን ሊያውክ የሚችለውን ጉዳይ ማረም እና መከላከል እንደሚገባ መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።
ከማኅበረሰቡ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ወንድም ወንድሙን መግደል አይገባም፣ የጋራ ጥያቄዎችን በጋራ መፍታት ሲቻል፣ በተለያየ ጎራ ተሰልፎ መጫረስ አሥፈላጊ አይደለም የሚል ሀሳብ ጎልቶ መውጣቱንም አንስተዋል።
አሁን ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በትኩረት እንሠራለንም ብለዋል። ሰላምን ለማጽናት የሕዝብ ትብብር እንደሚያስልግ ገልጸዋል። በከተማዋ የተገኘውን ሰላም ወደ ኋላ ለመመለስ ያልተገቡ ዝንባሌዎች መኖራቸውን ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከዚህ በኋላ ሰላምን ማሳጣት ሕዝብን ማጎሳቆል እንደሚኾንም ተናግረዋል።
በከተማ ያልተጨበጠ የሽብር ወሬ እየተዛመተ መኾኑንም ገልጸዋል። የሽብር ወሬ ከመንዛት አልፎ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቦንብ የማፈንዳት እንቅስቃሴ መኖሩን ነው የገለጸት። ሕፃናት በሚማሩበት ትምህርት ቤት ቦንብ ማፈንዳት አስነዋሪ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል። በልጆች አዕምሮ ላይ ያልተገባ ነገር ለመቅረጽ የሚደረግ ተግባር መወገዝ አለበት ብለዋል።
የከተማዋ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል ለማድረግ በከተማዋ መውጫ እና መግቢያ የሚገኙ ድልድዮች በፈንጅ እንዲፈርሱ የማድረግ ሙከራ መኖሩንም ገልጸዋል። የከተማዋ እና የክልሉ እንቅስቃሴ እንዲታወክ ለማድረግ የሚሠሩ አካላትን በጋራ ኾኖ ማረም ይገባል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ የሚያደርግ አካሄድ ትክክል ያልኾነ እና ጉዳቱ ከእስካኹኑ የባሰ እና አሰቃቂ የሚኾን መኾኑንም ገልጸዋል። ለአማራ ሕዝብ እቆረቆራለሁ የሚል ሁሉ ጭካኔ የተመላበት ድርጊት እንዲያወግዘውም ጥሪ አቅርበዋል።
ለአንድ ቀን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ቢታገድ ጦም አዳሪው ብዙ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰርቶ አዳሪዎች እንዳይጎዱ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም ይገባዋል ነው ያሉት። የከተማዋ የፀጥታ ኃይል ችግሮች እንዳይፈጠሩ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የሚኖረው እንቅስቃሴ ሰላማዊ እንዲኾን ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። የሃይማኖት አባቶች ለሰላም እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የከተማዋ ወጣቶችም ከተማዋን በመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ግጭት ምጣኔ ሃብትን ያወድማል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አንዳንድ ባለሀብቶች የባንክ እዳ መክፈል መቸገራቸውን፣ ሠራተኛ ለማሰናበት መገደዳቸውን አንስተዋል። ባለሀብቶች በሰላም ሃብት እንዲያፈሩ ለሰላም አውንተዊ ሚና እንዲጫወቱም ጠይቀዋል። ልማትን ሊያስተጓጉል የሚችልን አካሄድ በጋራ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!