የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

32

ጎንደር: ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠሩ የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በወረዳው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያለመ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ አመራሮች፣ ሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አሁን በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ጠቁመው ለዘላቂ ሰላም ሁሉም እየተረባረበ ስለመኾኑ አንስተዋል። የምክክሩ ተሳታፊዎች ለተፈጠረው የሰላም እጦት ዋነኛ መንስኤው ከአሁን በፊት ሲነሱ የነበሩ ያልተመለሱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መኾናቸው ጠቁመዋል።

ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ልክ አለመኾኑ፤ የሙስና እና የብልሹ አሠራሮች መስፋፋት፤ ሕዝቡ በበቂ ሁኔታ በፍትሕ ሥርዓቱ ተጠቃሚ አለመኾኑ እንዲሁም የአማራ ሕዝብ ከአሁን በፊት ሲያነሳቸው የነበሩ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች በወቅቱ መልስ አለማግኘታቸው ውለው አድረው አሁን ለሚታየው የሰላም እጦት ምክንያት መኾናቸውን ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች ያነሱት።

በወረዳው ብሎም በክልሉ እየተፈጠረ ያለው የሰላም ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የተናገሩት የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት እና ሕዝብ የድርሻቸውን ቆጥረው መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

የሰላም እጦቱ በሰው ሕይዎት እና በንብረት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ተገቢ አለመኾኑን አንስተው ለሰላም መስፈን በትኩረት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አላምረው አበራ በወረዳው እየተነሱ ያሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ቅድሚያ ለሰላም ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

መንግሥት እየታዩ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ እየሠራ መኾኑን የጠቆሙት አቶ አላምረው ሕዝቡ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር መሥራት አለበት ብለዋል።

በተለያዩ ሁኔታወች ተደናግረው ለወጡ ሁሉ መንግሥት በምህረት እንዲገቡ እየሠራ ነው ያሉት አቶ አላምረው ማኅበረሰቡ በተለይ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ- ኃይሉ ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ 392 ሚሊዮን ብር በኾነ ወጭ የጽዳት እና ውበት ሥራ እየተካሄደ ነው።
Next articleአሁን ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በትኩረት እንደሚሠራ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።