
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ በ392 ሚሊዮን ብር የተጀመሩ የጽዳት እና ውበት ሥራዎች እየተካሄደ መኾኑ ተገልጿል። ሥራዎቹ በመጪው ጥር ወር ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም የከተማ አሥተዳደሩ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ገልጿል።
የከተማ አሥተዳደሩ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ይርጋ አለሙ እንደተናገሩት በግንባታ ላይ የሚገኙት የጽዳት እና ውበት ሥራዎች 83 ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ የባሕር ዳር ከተማን ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንደሚያስችሉ ኀላፊው አስታውቀዋል።
ግንባታዎቹ በዓለም ባንክ የከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳንቴሽን ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ እየተሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል የጋራ መኖሪያ ቤቶች “ሴፍቲ ታንኮሮች” እና የከተማዋን የፍሳሽ አወጋገድ የሚያዘምኑ ግንባታዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ከተማዋ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ተመራጭ እየኾነች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎችን ቁጥር ታሳቢ ያደረጉ በመኾናቸው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል።
የጽዳት እና ውበት ሥራ ፕሮጀክቶቹ ግንባታ እየተካሄዱ ያሉት በገበያ አካባቢዎች፣ በመናኸሪያዎች እና ሰዎች በብዛት በሚኖሩባቸው ስፍራዎች መኾናቸውን ተናግረዋል። በተለይ የከተማዋን ጽዳት ለማስጠበቅ የፕሮጀክቶቹ መገንባት ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በአገልግሎቱ የሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አስተባባሪ ተስፋው አካልነው የባሕር ዳር ከተማን የጽዳት እና ውበት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በውጭ ኩባንያ ጥናት መካሄዱን ስለመግለጻቸው ኢዜአ ዘግቧል።
በጥናቱ ግኝት መሰረትም 83 የጽዳት እና ውበት ሥራ ፕሮጀክቶች ግንባታ በግንቦት/2015 ዓ.ም መጨረሻ እንደተጀመሩ ጠቅሰው አሁን ላይ ግንባታቸውን ከ75 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ እስከ ጥር/2016 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡም ለተደራጁ ወጣቶች በማስረከብ በአነስተኛ ክፍያ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል።
በቀጣይም የከተማዋን የሳንቴሽን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥናቱን መሰረት በማድረግ እንደሚሠራም አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!