
ደሴ: ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አራተኛ ዙር የመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ ሥልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ አመራሮች የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተመለከቱት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የያዘችውን እቅድ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደምትችል ማሳያ እንደኾነ ሠልጣኞች ገልጸዋል።
ሠልጣኝ አመራሮች በሥልጠናው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር በልዩነት እና በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ትርክትን ለማስወገድ እና የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የሚስችል ዕውቀት እና ክሕሎት እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት፡፡ በየአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር በማስወገድ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንትን መሳብ ይገባልም ብለዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ የከተማው ሕዝብ እና አመራር የከተማውን ሰላም በመጠበቁ የአመራሮች ሥልጠና በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ሰላሙን ዘላቂ በማድረግ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ እንደሚሠራም አብራርተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የጥናት እና ምርምር ኀላፊ እንዲሁም የወሎ ሥልጠና ማዕከል አስተባባሪ ተተካ በቀለ “ሀገራዊ ሥልጠና መሰጠቱ ሁሉም የመንግሥት አመራሮች ተቀራራቢ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያስችል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንዲጎበኙ መደረጉ ሠልጣኞች ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ለኢንቨስትመንት እና ለኢንዱስትሪ ትኩረት ሰጥተው እንዲደግፉ ያነሳሳቸዋል ነው ያሉት፡፡
መንግሥትም የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰይድ አብዱ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!