
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት በዘለቀው ታላቅ ታሪኳ በአንድነት፣ በነፃነት፣ በፀና ብሔራዊነት፣ በሀገር ወዳድነት፣ ከራስ በላይ አሳቢነት በሚያውቁ ልጆቿ ትታወቃለች። ልጆቿ ለአንድነት በሚሠጡት ታላቅ ሀገራዊ እሳቤ ምክንያት ለዘመናት ተከብራ እና ታፍራ ኖራለች። መከራዎቿን እና መሰናክሎቿንም አልፋለች።
ይህች በአንድነት እና በፀና ብሔራዊነት የሚታወቁ ልጆች ያሉባት ሀገር ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ አንድንቷን የሚያናጉ፣ የልዩነት ስንጥሮችን የሚያሰፉ ፈተናዎች ገጥመዋታል። የቀደመውን መልካም እርሾ ደፍተው አንድነቷ የላላች ሀገር ለመመሥረት የጣሩ እና የሚጥሩ በርክተውባት ቆይተዋል። ይህ እሳቤ አሁንም አለ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገራዊ አንድነትን ያጠናክርልኛል፣ የነበሩ ችግሮችንም ይፈታልኛል ያለውን ሥልጠና ለመንግሥት አመራሮች እየሠጠ ነው። በሥልጠናው ውስጥ ያለፉ መሪዎችም አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ያጎላሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በባሕር ዳር ማዕከል ሥልጠናቸውን እየወሰዱ የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም የባሕር ዳርን መሠረተ ልማቶች በጎበኙበት ወቅት ሀገራዊ አንድነትን ማስቀደም አለብን ነው ያሉት።
ከኦሮሚያ ክልል ጅማ የመጡት ሙክታር ዝናቡ ወደ ባሕርዳር ሲመጡ በሕይወት አጋጣሚ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ባሕር ዳር ሲመጡ ቆንጆ አቀበባበል፣ ያማረ መስተንግዶ ጠብቆኛል ብለውናል። የአማራ ክልል ሕዝብ አስደናቂ ነው፤ ብዙ ይወራበታል፤ የጦርነት ቦታ ነው ይባላል፣ ሕዝቡ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ሰላም ፈላጊ፣ ለሰላም የሚተጋ መኾኑን አይቸበታለሁ ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብ ታላቅ ሕዝብ፣ ሀገሩን የሚወድ፣ ኢትዮጵያዊነት ያላበት መኾኑን አረጋግጫለሁ፣ በጣምም ተረድቻለሁ ብለውናል። ኢትዮጵያዊ በመኾናችን በጣም የኮራንበት ሰዓት አሁን ነው፤ በአንድ ሥልጠና ማዕከል ውስጥ ኢትዮጵያ አለች፣ ኢትዮጵያ ትታያለች፣ ከዳር እስከ ዳር የማናውቀውን አውቀናል፣ ያልሰማነውንም ሰምተናል፣ ይህ ደግሞ ልዩ አጋጣሚ ነው ብለውናል።
ኢትዮጵያዊነት ምን እንደኾነ የገባን አሁን ነው፤ ከዚህ በኋላ እንደ አንድ ቤተሰብ፣ በአንድ ቤት ውስጥ እንደምንኖር ሠዎች ኾነን እንድንሠራ የተረዳንበት ነው፣ ሥልጠናው ከአሁን በፊት የነበረውን አንድነት የሚያጠናክር፣ ይበልጥ የሚያስተሳስር እና የሚያስተሳስብ ነው ይላሉ።
ግጭቶች ሕዝብን እና ሀገርን አይወክሉም፣ ሀገር ከሚጋጩት እና ከግጭቶች በላይ ናት፣ ወደየመጣንበት ስንመለስ አንድ እንደሆን እንሰብካለን፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል መንቀሳቀስና መሥራት እንደሚችል ተገንዝበናል፣ እኔ ኦሮሞ ነኝ ነገር ግን አማራ ክልል ውስጥ መጥቼ መኖር እና መሥራት እችላለሁ፣ ምክንያቱም ሀገሬ ስለሆነ፣ አንድ አማራም ኦሮሚያ ሄዶ መኖር እና መሥራት እንደሚችል ነው የተማርነው፣ ኢትዮጵያ አንድ ስለሆነች አንድ ላይ ሆነን፣ በአንድነት ሀገራችንን ወደፊት እንወስዳለን ነው ያሉት።
ያለንን ሀብት በአንድነት ጠብቀን ሀገርን መጥቀም ይገባናልም ይላሉ። ችግሮቻችን በአንድነት በመፍታት በአንድነት ከፍ ማለት አለብን ነው የሚሉት።
ከሶማሊያ ክልል የመጡት ዴቃ አብዱልአዚዝ ግሩም አቀባበል፣ ግሩም መስተንግዶ ነው የጠበቀን፣ ሁሉም የሚደክመው እኛን ለማስደሰት ነውም ብለውናል። ለኢትዮጵያ ምሳሌ እንድንሆን፣ የኢትዮጵያን አንድነት እንድናረጋግጥ የሚያስችል እድል አግኝተናል፣ አንድነትን ተምረናል፣ አጅ ለእጅ ተያይዘን ማደግ ጠቃሚ መኾኑን በጋራ ተገንዝበናልም ብለውናል።
የተማርነውን እውን ለማድረግ እንሠራለን፤ ኢትዮጵያ ሰላሟን መጠበቅ አለባት፣ አንድነቷ ከፍ ከፍ ማለት አለበት ነው ያሉት። አብሮነት እና አንድነት የኢትዮጵያ መገለጫ ነውም ብለውናል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመጡት ጌታቸው ታዬ ከመኖሬያ ቀያችን ስንነሳ አካባቢው በሽብር ውስጥ እንዳለ፣ መንገዶች ሁሉ እንደተዘጉ ይነገር ነበር፣ ከመጣን በኋላ ያየነው ግን የተለየ ነው፤ እንግዳ ተቀባይነታቸው የሚገርም ነው፣ የተነገረን ሰላም የለም ነው፣ ያየነው እና የተረዳነው ግን ሰላምን ነው ብለዋል።
ሥልጠናው ኅብረ ብሔራዊነት እና አንድነት ለማጠናከር ያግዛል፤ ኢትዮጵያ የአንድነት ሀገር ናት፣ የሚያምርባት እና የምትገለጥበት አንድነት እና ሕብረ ብሔራዊነት ነው ይላሉ። አሉባልታዎች አንድነትን ያቀጭጫሉ፣ ሕዝብን በጥርጣሬ ያሳያሉ፣ ከአሉባልታ በመራቅ እውነትን ይዞ ለሀገር አንድነት መሥራት ይገባናል ነው ያሉት።
ሐሰተኛ ወሬን መታገል እና የሕዝብን እውነታ መረዳት፣ ከእውነት ጋር መቆም፣ ለእውነትም መታገል ይገባል ብለዋል። ግጭቶችን በውይይት፣ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች መፍታት ይገባል ነው ያሉት። ሁላችንም ለሀገራችን ኢትዮጵያ ስንል ከእውነት ላይ እንቁም ብለዋል በመልእክታቸው።
ከአዲስ አበባ የመጡት ሀብታሙ ጋሻው ስለ አማራ ክልል የሚወራው እና መሬት ላይ ያለው እውነት የተለያየ ነው፣ ሕዝቡ ደግና እንግዳ ተቀባይ ነውም ብለውናል።
ከሁሉም ኢትዮጵያ ተውጣጥቶ በአንድ ላይ መሠልጠን አሁን ያለውን ሀገራዊ ኹኔታ ለመረዳት፣ በየአካበቢው ያለውን ሀገራዊ መረዳት ለማወቅ አግዞናል ነው ያሉት። ሥልጠናው የነበረውን አመለካከት የቀየረ በደንብ እንድንተዋወቅ ያደረገ፣ በሀገራዊ እሳቤዎች ላይም ያግባባን ነው ይሉታል።
ግጭቶች የግል ፍላጎት ውጤቶች ናቸው የሚሉት ሀብታሙ የጋራ አንድነትን በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባናል ነው የሚሉት። የግል ፍላጎትን መነሻ በማድረግ ሕዝብን ሰላም መንሳት አይገባም፤ ችግሮችንን በውይይት በመፍታት የሕዝብ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት ግርማው ጌቻሞ የባሕር ዳር ሕዝብ ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚኖር መኾኑን አይተናል ይላሉ። አቀባባል፣ አክብሮት፣ ኢትዮጵያዊነትን አይተናልም ብለውናል።
ጠቃሚ የሆኑ እሳቤዎችን በመያዝ፣ ብሔራዊነትን መሠረት ያደረገ አካሄድ መሄድ ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያዊነት አንድነት የሚያጠናክር፣ አቅምን የፈጠረ፣ አዲስ አስተሳሰብ የያዘ ሥልጠና መኾኑንም ነግረውናል።
የግጭቶች መነሻ ምክንያት አሉታዊ ትርክት ነው፣ አሉታዊ ትርክት ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ያላላል፣ አሉታዊ ትርክትን መተው፣ አወንታዊ ትርክቶችን ማጎልበት የተገባ ነው ብለውናል። ሥልጠናው በሀገር የሚታዩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል። አሉታዊ አስተሳብን ማረም፣ ሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊነትን ማሳደግ ይገባል ይላሉ።
ሁሉንም ሕዝብ አንድ የማድረግ እና የማስተሳሰር አደራ አለብን፣ የዘመናት ችግሮችን በውይይት መፍታት ይገባልም ብለውናል። ብሔራዊነትን እና አንድነትን ማረጋገጥ ከተቻለ ሀገር ተስፋዋ ብዙ ነው ብለዋል።
በፌዴራል መንግሥት የባሕር ዳር ሥልጠና ማዕከል አሥተባባሪ ደስታ ብዙአየሁ የመንግሥትን አመራር አቅም ማሳደግን ዓላማ ያደረገ ሥልጠና መሠጠቱን ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የመለያየት ትርክት እንደተተረከባት የገለፁት አሥተባባሪው ለዘመናት የቆዬው የመለያየት ትርክት አሁን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፣ ይሄን ችግር መቀየር፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን ማጉላት፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የማድረግ ትርክት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሠልጣኞችን የቆዬውን አፍራሽ ትርክት በማረም ሕብረ ብሔራዊነትን ይዞ ኢትዮጵያዊነትን አጠናክሮ እንዲሠሩ ተልዕኮ እንደሚሠጣቸውም ነግረውናል። ኢትዮጵያን የሚያውቁ፣ ኹኔታዎችን የሚረዱ እንዲኾኑ ይፈለጋል ነው ያሉት። ብቃት ያለው መንግሥት የመፍጠር ዓላማ የያዘ መኾኑንም ገልፀዋል።
በዘመናት ውስጥ ጥላቻ እንዲነግሥ፣ ፀብ እንዲጠመቅ ተሠርቷል የሚሉት አሥተባባሪው ይህንን ማረም እና የሕዝብን አንድነት ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። መሪዎች የሕዝባቸውን ጥያቄ ተረድተው መፍታት እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸውንም አንስተዋል።
ዘጋቢ: ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!