
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር 9ሺህ 190 ኩንታል የማር ምርት መሰብሰቡን የአሥተዳደሩ የእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለንብ ማነብ ምቹ የሆነ መልክዓ ምድርና የተፈጥሮ ፀጋ መኖሩን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሲሳይ አያሌው እንደተናገሩት በአሥተዳደሩ በንብ መንጋ ከተሞሉ ከ100 ሺህ በሚበልጡ ባሕላዊ እና ዘመናዊ ቀፎዎች በበጀት ዓመቱ ከ13ሺህ ኩንታል በላይ የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 9ሺህ 190 ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የማር ምርት በዘርፉ እየተሳተፉ በሚገኙ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና ባለሀብቶች መሰብሰብ ችለዋል ብለዋል።
በአካባቢው የሚገኙ ለንብ ተስማሚ የሆኑ ሀገር በቀል እፅዋት የዋግ ማር የተለየ መልክና ጣዕም እንዲኖረው ማስቻሉን አስረድተዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በስፋት የሚስተዋለውን የንብ ማነብ ሥራ በዘመናዊ መልክ ለማልማት መንግሥት ከሚያደርገው እገዛ ባሻገር በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአካባቢው ወጣቶች ልምድ እየሰጡ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
በሰቆጣ ወረዳ በንብ ማነብ ሥራ ላይ የተሰማራው “ጉዳየ” የተሰኘው አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር ተወካይ አቶ ደሳለኝ ታደሰ እንዳሉት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በለማ ተፋሰስ ንብ በማነብ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ዘመናዊ ቀፎን በመጠቀም በንብ መንጋ የተሞሉ 200 ቀፎዎች እንዳላቸው ጠቅሰዋል። እስካሁንም 1ሺህ 812 ኪሎ ግራም የማር ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮችን ከባሕላዊ ወደ ዘመናዊ ቀፎ በማሸጋገር ልምድ እንዲወስዱ እያገዙ መሆናቸውን አውስተዋል። ለ11 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አመልክተዋል።
ከግብርና ሥራቸው በተጓዳኝ በንብ መንጋ የተሞሉ ሁለት ዘመናዊና ሦስት ባሕላዊ ቀፎዎችን አዘጋጅተው እየሠሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ሹመት ስጦታው ናቸው።
እስከሁን ባደረጉት እንቅስቃሴ 15 ኪሎ ግራም ማር መሰብሰባቸውን እና ከማር ምርት ሽያጭም የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብልው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
በአካባቢው ቀደም ሲል የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ ለንብ ማነብ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ጠቅሰዋል። በቀጣይ የዘመናዊ ቀፎዎችን ቁጥር ለማሳደግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፈው ዓመት 9ሺህ 992 ኩንታል የማር ምርት መሰብሰቡን ከእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት ጽሕፈ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!