
ባሕር ዳር: ኅዳር 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት አመራር 4ኛ ዙር ሠልጣኞች የሚሳተፉበት ሥልጠና ለኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ ግንዛቤ እና አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊ አቶ ሶሪ ገዳ ”ሥልጠናው ከነጠላ ትርክት ወደ ጋራ ትርክት ተሻግረን ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የምንሻገርበት ነው” ብለዋል።
ሥልጠናውን ለመተግበርም ቁርጠኛ መኾናቸውን እና በየሄዱበት ሁሉ በመከባበር ለምትመሠረት ኢትዮጵያ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ሌላዋ ሠልጣኝ ወይዘሮ ኢክራም ሳልሃዲን ሥልጠናው ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
አሁን ላይ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያስተሳስር ትርክትን ይዘን ለመሥራት ነው የምንሠለጥነው” ብለዋል።
ሥልጠናው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት የመጠራጠር ስሜትን የሚያስወግድ እንደኾነም ተናግረዋል።
ሌላዋ ሠልጣኝ ወይዘሮ ማሪያ ቱፋም ”የተሰጠን ሥልጠና ከተለያየ አመለካከት ወደ አንድነት የሚያመጣን ነው” ብለዋል።
ሀገሪቱ የባሕል፣ የሃይማኖት እና የማንነት ብዝኃነት ያለባት መኾኗን ተገንዝበን በመከባበር ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመገንባት መሥራት እንዳለብን የተግባባንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የተሠሩ የልማት ሥራዎችን የጎበኙት ሠልጣኞቹ የባሕር ዳር ሕዝብ ጨዋ እና እንግዳ ተቀባይ መኾኑን መስክረዋል።
ባሕር ዳር ከተማ እየለማች መኾኗን እና ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱም ለተመሳሳይ ልማት እንደሚተጉ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!