
ባሕር ዳር: ኅዳር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ የትምህርትን ተደራሽነት እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ከሚንቀሳቀሱ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ጋር በአፈጻጸማቸው ዙሪያ እየተወያየ ነው። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ቢሮው የትምህርት ተደራሽነትን፣ አግባብነትን እና ጥራትን የሚያግዙ ስትራቴጂካዊ እቅዶችን በመለየት የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው ብለዋል።
ተቋሙ እነዚህን እቅዶች በአግባቡ ተግባሪዊ ለማድረግ የሚጠቀምባቸው ሰባት እስትራቴጂካዊ ግቦች እንዳሉትም ተናግረዋል። ግቦቹን ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ጥራትን በማምጣት ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚያግዙ በተለያየ አግባብ የተቋቋሙ አጋዥ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ተቀራራቢ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ ተገቢ መኾኑንም አንስተዋል። ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በቢሮ እና በመስክ መገምገሙንም ጠቁመዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የዓለም ባንክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሕጻናት መርጃ ድርጅት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ነው ያሉት። እነዚህ ፕሮጀክቶች እና ፕሮግራሞች ወጥ አፈጻጸም ካለመኖር በተጨማሪ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደነበሩባቸው ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የነበሩ ችግሮች ከዓመት ዓመት እየተቀረፉ የመጡ ቢኾንም ሀብትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የግዢ እና የኮንትራት ሥራዎች በወቅቱ አለመጠናቀቅ፣ ተከታታይ ድጋፍ አለማድረግ እና የአመራር ትኩረት ማነስ ዋና ዋናዎቹ ችግሮች እንደነበሩ ጠቁመዋል።
በተለይም የተመደበን በጀት በጊዜ የለኝም መንፈስ በአግባቡ አለመፈጸም የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ በሕጻናት ትምህርት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ የተለያዩ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች እቅድ አፈጻጸማቸውን ለታዳሚዎቹ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፕሮግራም ለፍትሐዊነት የእቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ ታከለ እያሱ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፕሮግራም ለፍትሐዊነት ፕሮጀክት ለአራት ዓመት የሚቆይ ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ የትምህርትን ውስጣዊ ብቃት ተደራሽነትን በማምጣት በኩል ድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በመጀመሩ የተማሪዎች ማቋረጥ እና በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል። ለፕሮግራሙ በዚህ ዓመት 830 ሚሊዮን ብር እንደተመደበ የጠቀሱ ሲኾን 715 ሚሊዮን ብር በጦርነት ለወደሙ አካባቢዎች መልሶ መቋቋም እንደሚውልም ጠቁመዋል።
በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊዎች እና ምክትል ቢሮ ኀላፊዎች፣ የትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊዎች፣ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!