
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ሂደት እና የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው። ውይይቱ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተወካዩች፣ የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አጋር አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ከተሜነት ይዟቸው የሚመጡ እድሎችን እና አደጋዎችን በአግባቡ ለይቶ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ፤ እንደ ደብረ ብርሃን ያሉ ከተሞች የኢንዱስትሪ፣ የእውቀት እና አዳዲስ ችግር ፈቺ ፈጠራዎች መገኛ እንደመኾናቸው ነገን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን ማቀድ እና መተግበር ይገባል ብለዋል። ቢሮ ኀላፊው በክልሉ 683 በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙና ስምንት ሪጆኦፖሊታን ከተሞች ቢኖሩም መዋቅራዊ ፕላኖቻቸው ነገን ታሳቢ ያላደረጉ መኾናቸውን በክፍተት አንስተዋል።
በአጠቃላይ የክልሉን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ለመፍታት ከተሜነት አይነተኛ መፍትሄ መሆኑንም ነው ዶክተር አሕመዲን የገለፁት። የስማርት ሲቲ ምንነት፣ አስፈላጊነት እና አተገባበር ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናቶች በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!