
አዲስ አበባ: ኅዳር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ተኛዉ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “ብዝኀነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት “በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በፓናል ዉይይት እየተከበረ ነዉ። በበዓሉ የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችና ከፍተኛ የመንግሥት ኀፊዎች ተገኝተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባዔ ዘሐራ ዑመድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲወስን ለዘላቂ ሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለዉን ድርሻ ከግምት በማስገባት ነዉ ብለዋል። በዓሉ ኢትዮጵያውያን ባሕልና ወጋቸዉን የሚያስተዋዉቁበት እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የተለያዩ ሥራዎች የሚከናወኑበት ነዉ ሲሉም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቃድር የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብት መከበር ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት ቀን ነዉ ብለዋል። ቀኑ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትም የሚያረጋግጥ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸዉ ድርሻ በአግባቡ ባለመሰነዱ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆይተዋል፤ እነዚህን የተሳሳቱ ትርክቶች ማረም ደግሞ የሁሉም ኀላፊነት መሆኑን አመላክተዋል። ዕለቱን በማስመልከት የፓናል ዉይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያግዛሉ የተባሉ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ዘጋቢ:- ኤልሳ ጉኡሽ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!