
ሰቆጣ: ኅዳር 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች መኖሪያ የኾነችው ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ናት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠሟትንም ፈተናዎች ለማለፍ በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ የሰቆጣ ከተማ የሃይማኖት አባቶች ተናግረዋል።
የሰቆጣ ወረዳ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ መልዓከ ፀሐይ ቀሲስ ይትባረክ አደረ እንደገለጹት ያለ ሰላም የሚጀምር ስብከትም ጸሎትም የለም። ሰላምን ቤተ ክርስትያን ለዘመናት ሰብካለች፤ አሁንም ከመስበክ አታቋርጥም፤ ወጣቱ ትውልድም የአባቶቹን ምክር በተግባር ሊገልጽ ይገባል ብለዋል።
መልዓከ ፀሐይ የሃይማኖት “ልዩነት ሳይኖር ተቻችለን እንደምንኖር በመጽሐፍ ቅዱስ የተመሰከረልን ታላቅ ሕዝቦች በመኾናችን አንዱ የአንዱን ባሕል እና ቋንቋ ሊያከብር ይገባል” ብለዋል።
የእስልምና ሃይማኖት መምህር የኾኑት ሼኽ ኑር ሙሐመድ ሰላም ለሀገር እድገት መግቢያ በር፤ ለሃይማኖት አባቶች የማስተማሪያ ርእስ እንደኾነ አስገንዝበዋል። ሼኽ ኑር በተለይ ወጣቱ ትውልድ ምክንያታዊነትን ምርኩዝ በማድረግና በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ኢትዮጵያን ከገባችበት ፈተና ሊያወጣት ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!