
ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የወጣቶች ሚና ለሰላም ግንባታ በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ወቅታዊ ኹኔታና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የመልካም አሥተዳደር፣ የኑሮ ውድነት እና የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች አሳስበዋል።
መንግሥት ከወጣቶች ጋር በቅርበት መሥራት ከቻለ ወጣቶችም በሁሉም ዘርፍ እንደሚተባበሩ ተናግረዋል።
የአካባቢው ወጣት የሰላምን አስፈላጊነት እና የጦርነትን አስከፊነት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የገለጹት ተሳታፊዎቹ ውይይቶችን በማጠናከር እና ሕዝብን የሚያሳስቱ መረጃዎችን በማጥራት መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) “የኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች ከጸጥታ ኀይሉ እና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለከተማዋ ሰላም መኾን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነው” ብለዋል።
ወጣቶች ለሀገር ሰላም ሚናቸው ከፍ ያለ መኾኑን ገልጸው ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ከክልል የሥራ ኀላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!