
ባሕር ዳር: ሕዳር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል” በሚል መልዕክት የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን እየተከበረ ይገኛል።
በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታህሳስ 1 የሚከበረው የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በኢትዮጵያም የጤና ሚኒስትር ከፍተኛ አመራሮች እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር አካለት በተገኙበት እየተከበረ ነው።
ዩ ኤን ኤድስ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፍራንሲዎ ናይሽሚ (ዶ.ር) ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ማኅበረሰቡ እና መንግሥት እንዲኹም አጋር አካላት በመተባበር የኤች አይ ቪ ኤድስን መሥፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ መግታት መቻሉን ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ 2022 በዓለም ዙሪያ 39 ሚሊዮን ሰዎች ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ይኖራል። 630 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል። በየዓመቱ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች በ2022 ተይዘዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ 610 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል። 11 ሺህ 320 በላይ ዜጎች ሕይዎታቸው አልፏል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አጋር አካላት እና መንግሥት በመተባበር ጥሩ መከላከል ቢኖርም አሁንም ግን የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲጋ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።
በመደጋገፍ እና በትብብር መሥራት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች ብለዋል። በአሁኑ ጊዜም በ6 ክልሎች የተለየ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ የገለጹት አምባሳደሩ ይህንን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ዘጋቢ:- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!