
ባሕር ዳር: ሕዳር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን በማስመልከት በሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት የፖናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
በውይይቱ በሀገራዊ አንድነት ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች እና ከወጣቶች ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በምክክሩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ሰይፈ ሞገስ የበለጸገች እና አንድነቷ የጠነከረ ሀገር ለመገንባት ወጣቱ ትውልድ ለሰላምና ለልማት ቅድሚ ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሰለጠኑ ሀገራት ዛሬ ከደረሱበት እድገት ለመድረስ በርካታ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና በምክክር ስለፈቱ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
አቶ ሰይፈ “እኛም ከአደጉ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ለልማት እና ለዴሞክራሲ ግንባታ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባናል፤ ይህንንም ዛሬውኑ እንጀምረው” ብለዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገው ወጣት አክሊሉ ወልዴ የዚህ ዓመት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለወጣቶች በብዙ መንገድ ሊያስተምር የሚችል በዓል እንደኾነ ተናግሯል።
ወጣት አክሊሉ “ወጣቱ ትውልድ ጉልበቱን ለልማት እና ለሰላም ካዋለ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን” ነው ያለው።
ደም በመለገስ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ያከበሩት ወይዘሮ በርነሽ ታደሰ “በተለያዩ ምክንያቶች ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን ደም በመለገስ ልናስባቸው ይገባል”ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!