
ባሕር ዳር: ሕዳር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው፡፡
ግምገማውን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ “የነገ ሀገር ተረካቢ ትዉልድ መፍጠር የሚቻለዉ ጤናማ ትዉልድ መፍጠር ሲቻል ነዉ” ብለዋል፡፡
ኅላፊው የማኅበረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የጤና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ትልቁን ድርሻ የሚዎስዱ በመኾኑ ጤና ተቋማት የሚጠበቅባቸዉን ኀላፊነት መወጣት አለባቸዉ ብለዋል።
በክልሉ በተፈጠረዉ ጦርነት ሕጻናት፣ እናቶች እና ተጎጅ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት ለማግኘት ተቸግረዉ ቆይተዋል ነዉ ያሉት።
በመንገዶች መዘጋጋት ምክንያት መድኃኒቶችን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ እንቅፋት መፍጠሩንም አንስተዋል። ከሐምሌ ወር ጀምሮ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ መቆየቱን የጠቀሱት ቢሮ ኅላፊዉ በሩብ ዓመቱም የወባ ታማሚዎች ቁጥር መጨመሩን አንስተዋል። በዚህም የወባ የሕሙማን ቁጥር ከ23 በመቶ በላይ ጨምሯል ነዉ ያሉት።
ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር የጤና ባለሞያዎች እና ባለድርሻ አካላት መናበብ እና በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ አበክሮ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- አዲስ አለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!