“ ተፈጥሮ የለገሰችው በረከት፣ ያልተነካው ሕብስት”

81

ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብልሆች የተሰጣቸውን በጥበብ እየተጠቀሙ ዘመናቸውን ይዋጃሉ፤ ከዘመናቸው እየቀደሙ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ በረከት ያስቀምጣሉ፣ በዓለሙ ፊት ኮርተው ይታያሉ፡፡ ያላቸውን በረከት፣ ተፈጥሮ የሰጣቸውን ስጦታ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ያወቁትን በሚገባውም መንገድ ይጠቀማሉ፡፡

ያላቸውን ያልተጠቀሙት፣ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ገጸ በረከት ያልፈተሹት ደግሞ ዘመኑን ከዋጁት ኋላ ይቀራሉ፡፡ ዘመናቸውን በድህነት ያሳልፋሉ፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለልጅ ልጆቻቸው የሚጠቅም ጥሪት ማካባት ሲችሉ ለራሳቸውም ሳይኾኑ ይቀራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ጸጋዎች የበዙላት፣ ተፈጥሮ አሳምሮ እና ሞሽሮ የፈጠራት ሀገር ናት፡፡ ከተዋበው ተፈጥሮዋ በተጨማሪ ብልህ እና ጠቢብ ልጆቿ ያማረውን ሁሉ ሰርተውባት አልፈዋልና የተወደደች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በሰጣት ሀብት እና ባደላት ገጸበረከት ልክ ግን የተጠቀመች፣ ሃብቷን ለይታ ያደገች ሀገር አይደለችም፡፡

በውስጧ የከበሩ ማዕድናት እንደሚገኙ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ማዕድናቷን አሉ ከማለት የዘለለ አውጥታ አልተጠቀመችባቸውም፡፡ ከሀብት ላይ ሀብት፣ ከእድገት ላይ እድገት አልጨመረችበትም፡፡ በአማራ ክልል በርካታ የማዕድን ሀብቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ዳሩ አለ ከማለት አልፎ ሀብቱን መጠቀም ላይ ብዙ ይቀራል፡፡

ማዕድን ተፈጥሮ የለገሰችው በረከት ነው፡፡ ያልተነካም ሕብስት ነው፡፡ አብልቶ የሚያጠግብ ሕብስት ኾኖ ሳለ አልተቆረሰም፡፡ አልተቀመሰም፡፡

በአማራ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ይታየው ተስፋሁን እንደነገሩን በአማራ ክልል 40 የሚደርሱ የማዕድን አይነቶች በጥናት ተለይተዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ማዕድን፣ የኢንዱስትሪ ማዕድን፣ የከበሩ እና በከፊል የከበሩ ማዕድናት፣ ብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት እና የኢነርጂ ማዕድናት በክልሉ በጥናት የተለዩ ናቸው፡፡ እነዚህን ማዕድናት በተገቢው መንገድ ለመጠቀም እየተሠራ መኾኑንም ነግረውናል ፡፡ ባለሀብቶችም በማዕድን ሀብት ላይ የመሰማራት ፍላጎታቸው እየጨመረ ነው፡፡

በተለይም የስሚንቶ ፋብሪካዎች በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሠሩ መኾናቸውን ነው የነገሩን፡፡ በክልሉ ታላላቅ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ተጀምረዋል፤ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የስሚንቶ ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ እንደሀገር የገጠመውን የስሚንቶ እጥረት እንደሚቀንሱም ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

እንደ ኀላፊው ገለጻ በአማራ ክልል በከሰል፣ በብረት እና በሌሎች ማዕድናት ባለሀብቶች ፈቃድ ወስደው እየሠሩ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጡ ጥሬ እቃዎችን የሚያስቀሩ ሥራዎች እተሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊው በወርቅ እና በኦፓል ላይ ጥሩ መነሳሳት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ማዕድን ሰላም ይፈልጋል፤ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ለማዕድን ሥራው እንቅፋት መፍጠሩንም አመላክተዋል፡፡ ታላላቅ በሚባሉ የማዕድን ፋብሪካዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የማዕድን ሀብት በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡ ማዕድኖች ባሕላዊ በኾነ መንገድ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው አጠቃቀሙን ዘመናዊ ለማድረግ ከዪኒቨርሲቲዎች ጋር እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ እንደ ኀላፊው ገለጻ አሁን ያለው እንቅስቃሴ እና የባለሀብቶች ፍላጎት አበረታች ነው፡፡

ቢሮው በጥናት የተለዩ ማዕድኖችን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ላይ መሠማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም ሙሉ መረጃ እንደሚሰጡም ገልጸዋል፡፡ የባለሀብቶችን ጥያቄ በቀላል መንገድ እየፈቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ወስደው በማይሠሩ ባለሀብቶችም እርምጃ እንደሚወስዱ ነው የገለጹት፡፡

በማዕድን ሀብቱ ላይ ሊኖር የሚችለውን ሕገ ወጥነት የሚቆጣጠር አካል መኖሩንም ተናግረዋል፡፡ ሕገ ወጥነትን ማጥፋት ግን አዳጋች መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ክልሉ የበርካታ ማዕድናት ባለቤት መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው የማዕድን ሀብቱን በተገቢው ለመጠቀም ሰላም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ በስፋት እንዲመጡ ለሰላም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ባለሀብቶችም በማዕድን ሀብት ላይ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘርፉ በቅንጅት እና በአንድነት መሥራት ከተቻለ ለሕዝብ እና ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

በወሎ ዪኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ መምህር እና ተመራማሪ ሲሳይ አወቀ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ የተሻሉ ጥራት ያላቸው የፋብሪካ ግብዓቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በኦፓል ላይ ጥናት እንዳደረጉ የተናገሩት ተመራማሪው ሰፊ የኦፓል ምርት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል በኦፓል ምርት ምንም አለመጠቀሙንም ተናግረዋል፡፡

የኦፓልን ማዕድን ውጤታማ በሚያደርግ ደረጃ መጠቀም አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ የኦፓል ማዕድን ከቁፋሮ፣ ከገበያ ትሥሥር፣ ከእሴት መጨመር እና ከአካባቢያዊ ተጽዕኖ አንጻር ችግሮች እንዳሉበት ያመላከቱት ተመራማሪው ባሕላዊ አቆፋፈር ምርቱ እንዲባክን በር የሚከፈት መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ በብዙ ድካም የተገኘውን ማዕድን በአግባቡ አለመያዝም ለብክነት እንደሚያጋልጥ ገልጸዋል፡፡

ደካማ የሆነ የገበያ እንቅስቃሴ መኖሩ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እንዳይኾን እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡ የኦፓል ምርትን በሚገባው ልክ የማስተዋወቅ ሥራ አለመሠራቱንም አመላክተዋል፡፡

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖርም ሌላኛው ችግር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የሰለጠነ ባለሙያ አለመኖር እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንዳይቻል አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራውም ደካማ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

በማዕድን ሀብቱ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በትብብር መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፣ የስልጠና ተቋማት ማቋቋም፣ ራሳቸውን ከአደጋ የሚጠብቅ ስልጠና መስጠት፣ የገበያ ማዕከል ማቋቋም፣ ዘመናዊ የኾኑ ማሽኖችን ማቅረብ፣ ዘመናዊ የኾነ የማዕድን አወጣጥ ዘዴን መጠቀም፣ የጥቁር ገበያውን መቆጣጠር ማዕድኑን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ የመፍትሔ አማራጮች መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ወሎ ዪኒቨርሲቲ በኦፓል ምርት ተደጋጋሚ ጥናት ማድረጉን ያነሱት ተመራማሪው በጥናት የተረጋገጠውን የኦፓል ምርት ከሚያቀርቡ ሀገራት የተሻለ የኦፓል ምርት መኖሩንም አስታውቀዋል፡፡ በማዕድን ሀብቱ ስኬታማ እና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የበርካታ አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡

ኦፓሉ ብራንድ ወጥቶለት ለዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀርብ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ያለውን እምቅ ሀብት መጠቀም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እኩልነታችንን፣ አንድነታችንን፣ ሀገራዊ ሰላማችንን እና መከባበራችንን ለዓለም የምናሳይበት ሊኾን ይገባል” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አፈ ጉባኤ ፈንታይቱ ካሴ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቤልጅየም ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ።