
አዲስ አበባ: ኅዳር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሚወጡ ፖሊሲ እና ሕጎች የአካል ጉዳተኞችን መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲኾን መንግሥት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሠራ መኾኑን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የፊታችን እሁድ የሚከበረውን ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ32ተኛ ጊዜ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ግዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን የፊታችን እሁድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዲና አሶሳ ከተማ ላይ እንደሚከበር የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤሮጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በበዓሉ ላይ የተለያዩ ኹነቶች እንደሚኖሩ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
የሚወጡ ፖሊሲ እና ሕጎች የአካል ጉዳተኞችን መብት እና ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲኾኑ መንግሥት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር እየሠራ መኾኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች ለማስከበር ሁሉም በይመለከተኛል መንፈስ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!