ከ12 ሺህ 600 ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

42

ባሕር ዳር: ኅዳር 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2016 ዓ.ም 333 ሺህ 400 ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እየተሠራ ነው። ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ ከ250 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን መታቀዱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ ሰብል ባለሙያ ተሻለ ዓይናለም ነግረውናል። ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም ለማግኘት ታቅዷል።

ባለሙያው እንደገለጹት እስከ አሁን 91 ሺህ 200 ሔክታር መሬት እና 160 ሺህ አርሶ አደሮች ተለይተዋል። 43 ሺህ 640 ሔክታር መሬትም ታርሷል። ከዚህ ውስጥ 12 ሺህ 626 ሔክታር መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል። 81 ሺህ 560 አርሶ አደሮች ወደ ሥራ ገብተዋል።

የመስኖ ግንባታዎችን፣ የከርሰ ምድር እና የገጸ ምድር የውኃ አማራጮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አቶ ተሻለ ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ለመስኖ ልማት የሚያገለግሉ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች እና ሞተሮች በተለያዩ ተቋማት እና ፕሮጀክቶች ተሰራጭተዋል።

በምክረ ሃሳቡ መሠረት 625 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ባለሙያው ለዚህ የሚኾን በቂ ግብዓት ቀድሞ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል። ይሁን እንጅ አቅርቦቱን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ የጸጥታ ችግር ማጋጠሙን ገልጸዋል።

የስንዴ ምርት የዝናብ እና የሙቀት ችግር ካላጋጠመ በስተቀር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች መልማት እንደሚችል ባለሙያው ገልጸዋል። በክልሉ ደጋ እና ወይና ደጋ አካባቢዎች በመስኖ መልማት የሚችልን መሬት ሁሉ ስንዴ ማልማት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በሞቃታማ አካባቢዎችም ለስንዴ ልማት ሰፊ መሬት እና የውኃ አቅም እንዳለ አንስተዋል።

ከጥቅምት እስከ ኅዳር መጨረሻ ማሣን በዘር በመሸፈን እስከ ጥር መጨረሻ ምርቱን መሰብሰብ ያስፈልጋል ብለዋል። በዘር ወቅት ማለፍ ምክንያት ሰብሉ ወደ መጋቢት እና ሚያዚያ የሚደርስ ከኾነ በሙቀት ምክንያት የምርት መቀነስ እንደሚከሰት ነው ባለሙያው የገለጹት።

የአማራ ክልል ከ2 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ የመልማት አቅም እንዳለው የግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝቡን የዘላቂ ሰላም ባለቤት ለማድረግ ቀን ከሌሊት እንደሚሠሩ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ገለጹ።
Next articleግሎባል አሊያንስ ለጎንደር ዩኒቨርስቲ 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።