ሕዝቡን የዘላቂ ሰላም ባለቤት ለማድረግ ቀን ከሌሊት እንደሚሠሩ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ገለጹ።

85

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት እና በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ከውጭ እና ከውስጥ አካላት ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላም በማወክ የሕዝቡን ኑሮ ለማጎሳቆል ያለሙ አካላት የአማራ ክልል መሪዎችን በሙሉ ለማሸማቀቅ በርካታ ሙከራዎችን እያደርጉ መኾኑ ተጠቁሟል።

ድርጊቱ የክልሉን ሕዝብ መሪ አልባ የማድረግ ምኞት በመኾኑ መቆም አለበትም ተብሏል።

አሁን ያሉ አመራሮች በድሎት ውስጥ የሚኖሩ ሳይኾን ሕዝቡን ከገባበት የሰላም እጦት ችግር አውጥተው ወደ ዘላቂ ልማት ለማስገባት ሌት ተቀን የሚሠሩ ስለመኾናቸውም ተጠቁሟል።

አመራሮች ከሕዝብ ጋር ኾነው ሕዝቡን ከገባበት ችግር ለማውጣት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈሉ ስለመኾኑም በምክክሩ ተነስቷል።

ሃሳብ እና ውይይትን ገፍቶ በመሣሪያ የማመን አካሔድ ችግርን የሚፈታ ሳይኾን ክልሉን እና መላ ሕዝቡን ወደከፋ ችግር ውስጥ የሚያስገባ መኾኑ በተጨባጭ እየታየ ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል ጥያቄዎችን በውል ተረድተው መልስ ለመሥጠት እና ለማሠጠት ከሚሠሩ የሕዝብ አመራሮች ጥያቄውን ነጥቆ አስመላሽ በመምሰል ሕዝብን የሚያውኩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አመራሮቹ ተናግረዋል።

የአማራን ጥያቄ አስመልሳለሁ በሚል ሰበብ ሕዝብን ሰላም እየነሳ፣ እያሰቃየ እና መንገድ እየዘጋ ያለውን አካል ሕዝቡ ከአመራሮቹ ጋር ቆሞ መታገል መጀመሩ ውጤት እያስገኘ ስለመኾኑም ተነስቷል።

“ሕዝቡ ለሰላም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፤ ሰላም እንዲሰፍንም በየቦታው እየተወያየ ነው፤ ስለሰላም ለምን አወራህ ተብሎ በሰላም ጠሎች የሚሰቃይም እንዳለ ተረድተናል” ብለዋል አመራሮች በውይይታቸው።

ሕዝቡም ይህንን በውል በመገንዘብ፣ ራሱ ከወለዳቸው መሪዎቹ ጋር በመቆም፣ በማበረታታት እና ሲሳሳቱም በወጉ በማረም እና በመቀየር ሰላም እና አንድነቱን ማስጠበቅ አለበት ብለዋል አመራሮቹ።

ሕዝባችን በታሪኩ ከዚህ የባሰ ችግር ገጥሞት አያውቅም፤ ጨዋ የኾነውን ሕዝባችንን ሰላሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ እና ከተደቀነበት አደጋ ለማዳን ከሕዝቡ ጋር በመኾን እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

“መስዋዕትነትን ከፍለንም ቢኾን የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ልማት እናረጋግጣለን” ሲሉም ከፍተኛ አመራሮቹ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ13 ወረዳዎች ላይ የወባ በሽታ መከሰቱ ተገለጸ።
Next articleከ12 ሺህ 600 ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።