በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ13 ወረዳዎች ላይ የወባ በሽታ መከሰቱ ተገለጸ።

86

ጎንደር: ኅዳር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሽታውን ለመቆጣጠር ከ2 ሚሊዮን በላይ አጎበር ተደራሽ መደረጉን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል።

በዞኑ በሚገኙ አብዛኛው ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ የተከሰተ ሲኾን ወረርሽኙ ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል የታች አርማጭሆ ወረዳ እና ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ተጠቃሽ ናቸው።

የታች አርማጭሆ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ መሳፍንት ወርቁ ወባን ለመቆጣጠር በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት የሚያስፈልግ ቢኾንም በአራት ቀበሌዎች ብቻ ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የቅድመ መከላከል ዝግጁነት ኦፊሰር መንግሥቱ በሌ እንደነገሩን በወረዳው ከ30 ሺህ በላይ ነዎሪዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሽታውን ለመቆጣጠር እክል መፍጠሩን አንስተዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ገቢያው አሻግሬ በዞኑ በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሽታው መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከል በታቀደው ልክ ለመሥራትም ጥረት መደረጉን ነው ያስገነዘቡት፡፡ በዞኑ ከሚገኙ 15 ወረዳዎች መካከል በ13 ወረዳዎች በሽታው መከሰቱን ነው ያረጋገጡት።

የመድኃኒት አቅርቦት፣ የግንዛቤ ፈጠራ እና የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር እንከን ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ኀላፊው በችግር ውስጥም ቢኾን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በተገኙበት የተቋሙን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማም አካሂዷል።

ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕዝብን አቅም በመጠቀም በርካታ መሠረተ ልማቶችን እንገነባለን” አሸተ ደምለው
Next articleሕዝቡን የዘላቂ ሰላም ባለቤት ለማድረግ ቀን ከሌሊት እንደሚሠሩ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ገለጹ።