
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር የአውራ ወረዳን የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት እና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
በሁመራ ከተማ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ እና የውይይት መርሐ ግብር ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው ተወላጆች እና የዞኑ አልሚ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ነጻነቱን ለማግኘት የሕይወት መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰው ያገኘነውን ነጻነት በማጽናት አካባቢያችንን ለማልማት በቁርጠኝነት እንሠራለን ብለዋል።
የዞኑ ባለሃብቶች ከነጻነት ማግሥት በተሠሩ መሠረተ ልማቶች ላይ ላደረጉት ድጋፍ አመሥግነው ለተጀመረው የአውራ ወረዳ የመንገድ መሠረተ ልማት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ከነጻነት ማግስት በሦስት ወረዳዎች እና በአንድ ከተማ አሥተዳደር በሕዝብ ተሳትፎ በቁርጠኝነት በርካታ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እንደተቻለ አስታውሰዋል።
ሕዝብ የማይነጥፍ ሃብት በመኾኑ በጀት የማይበግረው የሕዝብን አቅም በመጠቀም በርካታ መሠረተ ልማቶችን እንገነባለን ብለዋል።
በዞኑ “አንዲትም እናት በመንገድ እጦት መሞት የለባትም” ያሉት አሥተዳዳሪው በዞኑ በተለይም በወረዳዎች ያለውን የመሠረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ በተባበረ ክንድ በአንድነት እንሠራለን ነው ያሉት።
የአውራ ወረዳ የመንገድ ችግር በማኅበረሰቡ ዘንድ እያሳደረ ያለው ጫና የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው የተናገሩት የዞኑ አልሚ ባለሃብቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በዞኑ እየተሠሩ ባሉ መሠረተ ልማቶች ደስተኛ መኾናቸውን ያነሱት አልሚ ባለሃብቶቹ ለሦስት አሥርት ዓመታት የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ያልኾነው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።
በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ከባለሃብቶች ተሰብሰቧል።
የአውራ ወረዳን ከዳንሻ ከተማ የሚያገናኝ 60 ኪሎ ሜትር የመንገድ መሠረተ ልማት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መኾኑን የአውራ ወረዳ አሥተዳዳሪ በለው ነጋሽ ገልጸዋል፡፡
አቶ በለው ለመንገድ ግንባታው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!