
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለ2016/17 የምርት ዘመን ለመግዛት ከታቀደ 23 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እስከ አሁን ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በምርት ዘመኑ ከ23 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዷል።
እስካሁን 14 ነጥብ 79 ሚሊየን ኩንታል ኤን ፒ ኤስ ዝርያና ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ጠቁመዋል። ከተገዛው ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙን ገልጸዋል።
እስከ ታህሳስ ወር መጀመሪያ አካባቢ ተጨማሪ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ይደርሳል ነው ያሉት። በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ መንግሥት የዓለም ከፍተኛ የማዳበሪያ ጭማሪና የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ከግምት በማስገባት ከፍተኛ ድጎማ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ባለፉት ሦስት ዓመታት የ52 ቢሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!