“አብዛኞቹ የክልሉ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

98

ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት በክልሉ ወቅታዊ ኹኔታ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የውይይቱን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦት ችግር ተቀርፎ የሕዝቡ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ ሥራ እየተከናወነ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም የተቀናጀ ሥራ በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ ሕዝቡን የአስተማማኝ ሰላም እና ልማት ባለቤት ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። ሕዝቡም በየጊዜው መውጫ መግቢያ መንገዱን የሚዘጉ እና ሰላሙን የሚያውኩ አካላትን ልክ ያልኾነ አካሄድ በመረዳት ከመንግሥት ጋር እየተወያየ ለሰላሙ እየሠራ ስለመኾኑ ርእሠ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል።

ለክልሉ እና ለሕዝቡ ሰላም ደንታ በሌላቸው አካላት አጀንዳ ተጠልፈው ወደ አልባሌ የሁከት ድርጊት ውስጥ ገብተው የቆዩ ወጣቶች ሕዝብ እና መንግሥትን ይቅርታ እየጠየቁ እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። ውሎ አድሮም ቢኾን ጥፋታቸው የገባቸውን እነዚህን አካላት አመክሮ በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እና ጉልበታቸውን ለልማት ብቻ እንዲያውሉ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወንም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

ሕዝብን ያገለግላሉ ተብለው በሕዝብ ሃብት ከሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ የሕዝብን አደራ በመብላት ሰላሙን ሲያደፈርሱ ስለመያዛቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። ይህንን አካሄድ በሕግ አግባብ የማረም ሥራ ተሠርቷልም ብለዋል። እንዲህ አይነት የመንግሥት ሠራተኞች ከመላላክ እና ከአላስፈላጊ ውዥንብር ወጥተው ለሚከፍላቸው ሕዝብ በጽናት እና በሙሉ ጊዜያቸው መሥራት እንዳለባቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ አሳስበዋል።

በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ሕዝቡ የገጠመውን ችግር በውል በመገንዘብ ከዚህ ችግር ፈጥኖ ለመውጣት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ሁሉም አመራሮች ያለምንም ልዩነት በጋራ በመቆም የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ቀርፎ በሙሉ አቅም ወደ ልማት ለመግባት ሁሉም አመራሮች ከሕዝብ ጋር በመኾን እና ስለሕዝብ በማሰብ ሌት ተቀን መሥራት አለባቸው ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ “ሕዝብ ዘላቂ ሰላምን አጥብቆ ይሻል፤ ይህንን ሰላሙን ለማስመለስ ደግሞ ከመንግሥት ጋር ኾኖ እየሠራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ሰላምን ወደ ጎን በመተው ሕዝብን ሲያደናግሩ የነበሩ አካላትን በሕግ አግባብ በመያዝ ወደ ተሃድሶ ማዕከላት በማስገባት፣ ወንጀል የፈጸሙትን ደግሞ በሕግ የመጠየቅ ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።

በአመራርነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የሚከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም የምናረጋግጥበት ጊዜ ላይ መኾናችንን በመረዳት እና የጋራ አቋም በመያዝ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ሰላሙን አጥብቆ የሚሻ ሕዝብ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን ሰላም የሚያውኩ እና እረፍት የሚነሱ አካላትን በመከታተል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሕዝቡ ተሳትፎ እና ጥንካሬ ወሳኝ ነው ብለዋል።

📸 ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አመራሩ የሕዝቡን እርካታ በሚያረጋግጥ ኹኔታ በይበልጥ ውጤት ለማምጣት መትጋት አለበት” አቶ አደም ፋራህ
Next article“ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቷል” የግብርና ሚኒስቴር