
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ ሥራዎች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማዳኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገልጿል። የደብረ ብርሃን ከተማ ወጣት እና ስፓርት መምሪያ የ2015 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የ2016 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መክፈቻ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ በክረምት በጎ ፈቃድ እገልግሎት ላይ የደም ልገሳ፣ የአረጋዊያን ቤቶችን መጠገን እና አዲስ ቤቶችን መሥራት፣ ችግኝ ተከላ እና የአካባቢ ጽዳትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች ስለመከናወናቸዉ ተነግሯል።
በሌላ በኩል ከሰላምና ደኅንነት አኳያ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ስለመሥራታቸው ነዉ የተነገረዉ፡፡
በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ቤተሰብ ላላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍና የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እንዲሁም ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ መደረግ መቻሉም ተገልጿል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ስፓርት መምሪያ ኀላፊ አውራሪስ አረጋ ከፍያው የሕሌና እርካታ በኾነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 59 ሺህ ወጣቶች በክረምት የተሳተፋ ስለመኾናቸው ተናግረዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲከናወን የተለያዩ አጋር አካላትም መሳተፍቸው የተገለጸ ሲኾን ምሥጋና እና እውቅናም ተበርክቶላቸዋል።
ተግባሩን ወቅት ሳይጠበቅ በሁሉም ሁኔታዎች ላይ በማከናወን ወጣቶች ማኅበረሰብን ማገልገል መቻል እንዳለባቸውም ተገልጿል።
የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከክረምቱ ያላነሰ ተግባር ማከናወን ይገባል ተብሏል። በመርሐ ግብሩ የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ኾነዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!