የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የማነቃቃት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

81

ደሴ: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ታላሚ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል። “ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት፣ አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም” በሚል መሪ መልእክት የዓለም የቱሪዝም ቀን በደሴ ከተማ እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር መሐመድ በዓሉ በክልሉ ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን ያለመ ነው ብለዋል። በምሥራቅ አማራ እና አካባቢው በርካታ የቱሪዝም ሃብት እንዳለ ገልጸው ሰላሙን በማስጠበቅ ዘርፉን የሃብት ምንጭ እና ለወጣቶችም የሥራ እድል መፍጠሪያ መስክ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ሰላም ለቱሪዝም አስፈላጊ ነው ያሉት ኀላፊው በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ክልሉ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚያገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል። በዓሉን ከማክበር ባለፈ በደሴ ከተማ፣ በደቡብ ወሎ እና በአካባቢው ያሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች ለማደስ እንዲሁም ጥበቃ እና እንክብካቤ ለማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።

በበዓሉ ከምሥራቅ አማራ እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሥራ ኀላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ማሕሌት ተፈራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንደ ሀገር የሰላም እሴቶችን መገንባት እና ሰላም እንዲረጋገጥ መሥራት ይገባል ተባለ።
Next articleበክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማዳኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።