
አዲስ አበባ: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰላም ምክር ቤት ሁለተኛ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ከተመሠረተ ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው የሰላም ምክር ቤት የሰላም ግንባታ ሥራን ገምግሞ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ውይይት እያካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ.ር) ሰላም ሁለት ገጽታ የያዘ ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል። በአንድ በኩል ሰላም ልማትን ለማፋጠን፣ ዴሞክራሲን ለማስፈን እና መልካም አሥተዳደርን ለማረጋገጥ የአስቻይነት ሚና ይጫዎታል ነው ያሉት። ሰላም ከድኅነት ለመውጣት በሚደረገው ርብርብ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫዎትም አስገንዝበዋል።
ሰላም የልማት ተቋማት በፖሊሲ ማዕቀፎቻቸው እና በትግበራ ስልቶቻቸው በፕሮግራም እንዲሁም በዓመታዊ ዕቅድ በጥምረት ይዘው የሚያከናውኑት ተልዕኮ መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰላም በራሱ በግብነት ተይዞ የሚከወን እራሱን የቻለ ተግባር ነው ብለዋል። የሰላም ግንባታ ሥራ ፍሬያማ እንዲኾን ካስፈለገ ከሁሉም ለሁሉም በሚል መንፈስ ተቋማት ኀላፊነት ወስደው በባለቤትነት የሚከውኑት ቁልፍ የጋራ ተልዕኮ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
አሁናዊ የሀገሪቱ ሁኔታ በትኩረት ለተከታተለ እዛም እዚህም በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች ሕይዎታቸውን እያጡ፣ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው፣
ንብረታቸው እየወደመ እና ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ የእንግልት ኑሮ እየመሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ሚኒስትር ድኤታው ዜጎችን ከተጋረጠባቸው አደጋ ለመታደግ ለነገ የማይባል ፈጣን ምላሽ ይሻል ነው ያሉት፡፡ በተለይም ከሥነ ልቦና ቀውስ የሚፈውሱ ሥራዎች እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው እና በተለያየ ቦታ ተበትነው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ቀያቸው መመለስ ብርቱ ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ የሕዝብ ለሕዝብ መልካም ግንኙነት እና አብሮነት በመሻከሩ የንግድ፣ የማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስሮችን ወደ ነበረበት የመመለስ ጠንካራ ሥራ እንደሚጠበቅም ዶክተር ስዩም መስፍን አስገንዝበዋል።
ከድህረ ግጭቶች አንጻር ለተፈጠሩ ጉዳቶች ምላሽ ከመስጠት ጎን ለጎን አለመግባባቶች በሚታይባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የግጭት መከላከል እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ትኩረትን ይሻሉ ብለዋል፡፡
ግጭቶችን አስቀድሞ ከመከላከል አንጻር ትልቅ ሚና የሚጫወተው የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መጠቀም ሲኾን ከዝቅተኛው የመንግሥት መዋቅር እርከን እስከ ፌዴራል ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ በመኾኑ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ለሀገር ግንባታ ትልቅ ድርሻ ያለው ብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለብሔራዊ መግባባት እና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አጋዥ ሚና እንደሚጫዎት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተለያዩ አደረጃጀቶች እና ክልሎች ጋር የሠራቸው ሥራዎች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች እንዳሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!