
ሁመራ: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚገኙ የወረዳ አሥተዳደሮች ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የመሠረተ ልማት ግንባታ ተነፍጓቸው በርካታ ችግሮችን ሲጋፈጡ ቆይተዋል።
በወረዳዎች የመንገድ፣ የቤተ መጽሐፍት፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እና የገጠር ቀበሌን ከከተማ የሚያገናኝ መንገድ ባለመኖሩ ለ30 ዓመት የልማት ባይተዋር ኾነዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ከነጻነት ማግስት ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ ቢኾንም በኅብረተሰብ ተሳትፎ በ2015 በጀት ዓመት የውስጥ ለውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የቤተ መጽሐፍት ግንባታ፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታ እና የገጠር ቀበሌዎችን ከከተማ የሚያገናኝ የጠጠር መንገድ ገንብቶ በማስመረቅ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
አሁንም በዞኑ የአውራ ወረዳ ነዋሪዎች ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ የመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ባለመኾናቸው በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ አድርጓል።
ይህን የተረዱ የዞኑ ነዋሪዎች በአንድነት በመሰባሰብ የአውራ ወረዳ የመንገድ ችግርን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ለአውራ ወረዳ መንገድ ግንባታ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ የተሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በሁመራ ከተማ አካሂዷል ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “በነጻነታችን ክንድ የአካባቢያችንን መሠረተ ልማት በማጠናከር ሕዝባችን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾን እንሠራለን” ብለዋል።
የዞኑ ወረዳዎች ለበርካታ ዓመታት የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ባለመኾናቸው እናቶች በወሊድ ወቅት ለሞት ተዳርገዋል፤ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ወደ ገበያ አቅርበው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል ነው ያሉት።
“ከነጻነት ማግስት በጀት ሳይገድበን የአካባቢያችንን ኀብረተሰብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሠራለን” ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይጨርስ አይጀምርም እና በአውራ ወረዳ የተጀመረው የመሠረተ ልማት ግንባታ እንዲጠናቀቅ በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የልማት ወዳዶች በቁርጠኝነት ድጋፍ እንዲያደርጉም ኮሎኔል ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው “በተባበረ ክንድ ነጻነታችንን እንዳረጋገጥን ሁሉ የአካባቢያችንን ልማት በቁርጠኝነት ለማስቀጠል ለልማት ዘብ ልንቆም ይገባል”ብለዋል።
ተስፋ፣ እልህና ቁጭትን አንግበው የወረዳቸው ሕዝብ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾን በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም አስረድተዋል ።
የዞኑ ሕዝብ ለመሠረተ ልማት እያደረገ ላለው ድጋፍ እና ተሳትፎም ምሥጋና አቅርበዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችም በሥራቸው ለኅብረተሰቡ ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር የመሠረተ ልማት ግንባታው እስኪጠናቀቅ በገንዘባቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል ።
በአውራ ወረዳ 60 ኪሎ ሜትር ለሚካሄደው መንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከ923 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል።
ዘጋቢ – ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!