በሕፃናት ስብዕና ግንባታ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

25

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሩብ ዓመቱ ከ92 ሺህ በላይ ሕጻናት ድጋፍ መደረጉን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገልጿል።

ቢሮው ትኩረት አድርጎ ከሚሠራቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ የሕጻናት መብት እና ደኅንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ነው፡፡

በቢሮው የሕፃናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አሻግሬ ዘውዴ እንዳሉት በአማራ ክልል በየጊዜው በሚከሰቱ ግጭቶች እና በተለያዩ ምክንያቶች የተጋላጭ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በ2016 ዓ.ም ሩብ ዓመት ከ92 ሺህ 200 በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ሕጻናትን በመለየት በተለያዩ አማራጮች ተጠቃሚ እንዲኾኑ መደረጉንም ገልጸዋል።

ድጋፉ ማኅበረሰቡን በማስተባበር፣ ከተለያዩ አጋር አካላት በጊዜያዊ እና በቋሚነት ከተገኘ ድጋፍ እና ከሌሎች አማራጭ የሕጻናት ድጋፍ እና እንክብካቤ መርሃ ግብሮች የተገኘ ነው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በሩብ ዓመቱ 160 ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ ተሰርቷል። 28 ሕጻናት ደግሞ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ እንዲሰማሩ እና ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።

82 ሕጻናትም በማሳደጊያ ተቋማት ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ተመቻችቷል ተብሏል። አሁን ላይ ድርቅ እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በችግር ውስጥ የወደቁ ሕጻናትን የልየታ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

የሕፃናትን መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አለመኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በሕጻናት ስብዕና ግንባታ ላይ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበትምህርት ዘርፉ የሚደረገው የማሻሻያ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ።
Next article“በነጻነታችን ክንድ የአካባቢያችንን መሠረተ ልማት በማጠናከር ሕዝባችን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾን እንሠራለን” ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ