ከበጋ መስኖ ልማት 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ።

55

ባሕር ዳር: ኅዳር 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከበጋ መስኖ ልማት 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በ2015/16 የመኸር እርሻ ሥራ ከለማው አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካኹን በአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል ተሰብስቧል ብለዋል።

ሰሊጥ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተር እና የቢራ ገብስ በዘመናዊ እና በባሕላዊ መንገድ በመታገዝ የመሰብሰብ ሥራው በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን አስታውቀዋል። በክልሉ ሰፊ የምርት ሽፋን ያላቸውን የስንዴ፣ የጤፍና የበቆሎ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራም ተጀምሯል። በዘመናዊ መንገድ ለመሰብሰብ በክልሉ ከሚገኙ ባለሃብቶች እና ማኅበራት ኮባይነር የማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን በማስተባበር ተማሪዎችና መምህራን ለሰብል ስብሰባው እገዛ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከአንድ ሄክታር በአማካኝ 31 ነጥብ ሁለት ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል። በአጠቃላይ በክልሉ በዘር ከተሸፈነው መሬት 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

አቶ ቃልኪዳን በክልሉ የሚገኙ ቀድመው የደረሱ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾኑ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ወደተለያዩ ሀገራት መላክ መጀመራቸውን አመላክተዋል፡፡ በምርት ዘመኑ የግብዓት አቅርቦት፣ የጸጥታ መደፍረስ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም የዝናብ እጥረት ተግዳሮት እንደነበሩ አስታውሰዋል። አሁን ላይም ያለው የጸጥታ ሁኔታ ኮምባይነርን ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሶ ምርት ለመሰብሰብ ፈታኝ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመኖሩ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየተሠራ ነው ብለዋል። በየደረጃው ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ለግብርና ባለሙያዎች ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የሚቲዎሮሎጂ ትንቢያዎችን የማድረስ እና ዘመናዊ የመሰብሰቢያ መሣሪያዎችን ወደክልሉ የማስገባት ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው የበጋ ወቅትም ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በነባር እና በአዲስ የመስኖ አማራጮች በማልማት 40 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

በመስኖ ከሚለማው ጠቅላላ መሬት ውስጥ 250 ሺህ የሚሆነው በበጋ መስኖ ስንዴ የሚሸፈን ነው ብለዋል። 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይጠበቃልም ብለዋል። በሁሉም አካባቢዎች የበጋ መስኖ ሥራው ምን ላይ ማተኮር እንዳለበት እና እስከመቼ ይጠናቀቃል የሚለውን የጋራ ለማድረግ በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን አመላክተዋል።ኢፕድ እንደዘገበው 81 ሺህ ሄክታር መሬት የመለየት እና 37 ሺህ ሄክታር መሬት በማሳረስ ከዘጠኝ ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር እንዲሸፈን ተደርጓልም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በፆታዊ ጥቃት ላይ በሚመክረው መድረክ ለመካፈል ደቡብ አፍሪካ ገቡ።
Next articleባለፉት አራት ወራት ከ193 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።